አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በዓለም አቀፍ ደረጃ የሃሰተኛ መረጃ ሥርጭት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱ ተመላክቷል።
ሁለተኛው የሹሻ ዓለም አቀፍ የሚዲያ ፎረም በአዘርባጃን እየተካሄደ ነው፡፡
በፎረሙ “አሁናዊው የሃሰተኛ መረጃ ሥርጭት ተጽዕኖ” እና ሃሰተኛ መረጃዎችን መቋቋም የሚችል ማህበረሰብ መፍጠር የሚያስችሉ ፖሊሲዎች እና ኢኒሼቲቮች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
የአልጀዚራ ሚዲያ ኢኒሼቲቭ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሞንቲሰር ማሪ በፎረሙ ባደረጉት ንግግር÷የሃሰተኛ መረጃ ሥርጭት በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተበራከተ መምጣቱን አንስተዋል።
በተለይም ግጭቶች በሚከሰቱባቸው አካባቢዎች የሃሰተኛ መረጃ ፍሰት እና ሥርጭት እያሻቀበ መምጣቱን አስረድተዋል፡፡
በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የሚፈጠሩ ይዘቶችን የማጣራቱ ሒደት በመገናኛ ብዙሃን ላይ የተጣለ በመሆኑ የመረጃ ማጣራት ማዕከላትን በስፋት ማቋቋም እንደሚጠበቅ አመልክተዋል፡፡
በፎረሙ ላይ ከ150 በላይ ጋዜጠኞች፣ የመገናኛ ብዙሃን አመራሮች እንዲሁም የጥናትና ምርምር ተቋማት መሳተፋቸው ተጠቁሟል፡፡
በምስክር ስናፍቅ