የሀገር ውስጥ ዜና

የመዲናዋን መሰረተ ልማቶች በአግባቡ ለመጠበቅ የሚያስችል የደንብ ማስከበር ህግ ማሻሻያ ተደረገ

By ዮሐንስ ደርበው

July 24, 2024

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን በመዲናዋ የተሰሩ የመሰረተ ልማት ስራዎችን ከጥፋት ለመጠበቅ የሚያስችል የደንብ ማስከበር ህግ ማሻሻያ ማድረጉን አስታወቀ፡፡

የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለስልጣንና የአዲስ አበባ የፅዳት አስተዳዳር ኤጀንሲ ማሻሻያውን አስመልክቶ በጋራ በሰጡት መግለጫ፤ ማሻሻያው የለሙ ፓርኮች፣ ኮሪደሮች፣ መንገዶችና ተጓዳኝ ልማቶች የሚሰጡትን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ለማስጠበቅ እንደሚያግዝ ተገልጿል፡፡

የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ በወቅቱ እንዳሉት÷ የህግ ማሻሻያዎች መደረጋቸው የተገነቡትን መሰረተ ልማቶች በአግባቡ ለመጠበቅና ከጥፋት ለመታደግ እንደሚያስችል ተናግረዋል።

በዚህም ማንኛውም ሰው ያመነጨውን ደረቅ ቆሻሻ በግቢው ውስጥ በአግባቡ ያለመያዝና በአይነት ያለመለየት፣ ማዝረክረክ፣ ጤናና የአካባቢን ገጽታ በሚጎዳ መልኩ ማከማቸት 2 ሺህ ብር ያስቀጣል ብለዋል፡፡

ይህንኑ ተግባር ሲፈጽሙ የተገኙ ድርጅቶች ደግሞ እስከ 50 ሺህ ብር ይቀጣሉ ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ደረቅ ቆሻሻን ከግቢው አውጥቶ ባልተፈቀደ ቦታ ላይ የጣለ ወይም ያስቀመጠ በግለሰብ ደረጃ 2 ሺህ ብር የሚቀጣ ሲሆን ከኢንዱስትሪ የወጣ ቆሻሻ ከሆነ 50 ሺህ ብር ያስቀጣል፡፡

ከጤና ተቋማት ወጥቶ ባልተፈቀደ ቦታ የተቀመጠ ወይም የተጣለ ቆሻሻ 30 ሺህ ብር ከሌሎች ድርጅቶች የመነጨ ከሆነ ደግሞ 10 ሺህ እንደሚያስቀጣ በደንቡ ላይ ተቀምጧል፡፡

አሽከርካሪ ወይም ተሳፋሪ ከመኪና ውስጥ ሆኖ ማንኛውንም ዓይነት ደረቅ ቆሻሻ ወደ ውጭ ከጣለ 2 ሺህ ብር እንደሚቀጣ ተደንግጓል፡፡

በተመሳሳይ እግረኞች በህግ የተከለከሉ ቦታዎች ላይ የሚጥሏቸው የሲጋራ ቁራጮች፣ ሶፍትና መሰል የተለያዩ ማሸጊያ ወረቀቶችና የፍራፍሬ ተረፈ ምርቶች 2 ሺህ ብር ያስቀጣሉ፡፡

በተደረገው የህግ ማሻሻያ መሰረት በህገ ወጥ መንገድ ፈሳሽና ደረቅ ቆሻሻ የሚጥሉ ሰዎች ወይም ድርጅቶች ዝቅተኛው 2 ሺህ ብር ከፍተኛው ደግሞ 100 ሺህ ብር ቅጣት እንደሚጣልባቸው ተጠቁመዋል።

የአዲስ አበባ የፅዳት አስተዳዳር ኤጀንሲ ዋና ስራ አስኪያጅ እሸቱ ለማ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በህብረተሰቡ ሁለንተናዊ ተሳትፎ የተሰሩት ልማቶች በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውሉና በዘላቂነት ደህንነታቸው እንዲጠበቅ የህግ ከለላ ያስፈልጋል ብለዋል።

የቅጣት ማሻሻያ ከተደረገባቸው የደንብ መተላለፍ ህጎች መካከል በመንገድ ላይ መጸዳዳት፣ ከአትክልትና ፍራፍሬ ንግድ ማዕከላት ውጭ ወይም መንገድ ዳር የሚጣሉ ተረፈ ምርቶች፣ ከመኖሪያ ቤትና ከድርጅት ግቢ ውጭ ያለውን አካባቢ አረንጓዴ አድርጎ አለመጠበቅ መኪና ባልተፈቀደ ቦታ ማጠብ ወይም ማሳጠብ ይጠቀሳሉ፡፡

እንዲሁም በጫማ ጽዳትና ጥገና የተሰማሩ እንዲሁም በእረፍት ቀን ቅዳሜና እሁድ በመንገድ ንግድ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች እስከ አምስት ሜትር ያቆሸሹትን አካባቢ ካላጸዱ ቅጣት እንደሚጣልባቸው ተገልጿል፡፡