አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ለቀጣናው መረጋጋት እያበረከተች ያለውን ከተኛ ሚና ኖርዌይ አደነቀች፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ከኖርዌይ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቢየርግ ሳንዳጃር ጋር የሀገራቱን ዘርፈ-ብዙ ግንኙነት በይበልጥ ማሳደግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል፡፡
በውይይታቸውም በሀገራቱ መካከል ስላለው ጠንካራ አጋርነት በተለይም በትምህርት፣ ጤና፣ በአየር ንብረት ለውጥ እንዲሁም በሰላምና ፀጥታ ዙሪያ መምከራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡
እንዲሁም በተለያዩ የሁለትዮሽ፣ ቀጣናዊ፣ አኅጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ የጋራ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።
ያለውን ትብብር በይበልጥ ማሳደግ እንደሚገባ ያመላከቱት አምባሳደር ምስጋኑ÷ የኖርዌይ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጋብዘዋል፡፡
ሚኒስትሯ በበኩላቸው በሀገራቱ መካከል ያለውን ጠንካራ ወዳጅነት በማውሳት ኢትዮጵያ ለቀጣናው መረጋጋት እያበረከተች ያለውን ሚና አድንቀዋል፡፡