አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በመጠጥ ዘርፍ የተሰማሩ አልሚዎች በሥራ ሒደት በሚያጋጥሟቸው ተግዳሮቶች ላይ በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባ ተገልጿል።
በኢትዮጵያ በመጠጥ ኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሰማሩ አምራቾች ፎረም ተካሂዷል።
ፎረሙ በዘርፍ የተሰማሩ አልሚዎች ከገበያ ፉክክር ባለፈ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በትበብር እንዲሰሩ ለማስቻል ያለመ ነው ተብሏል።
በፎረሙ አሁን ላይ በኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚስተዋሉ መልካም እድሎች እና ተግዳሮቶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
በዚህም በመጠጥ ምርት የተሰማሩ ድርጅቶች ጤናማ የገበያ ፉክክር በመፍጠርና በትብብር በመስራት ምርታማነታቸውን ይበልጥ ማሳደግ እንደሚችሉ ተመላክቷል።
የሃይል አቅርቦት፣የጥሬ ዕቃ ግብዓት እጥረት፣የውጭ ምንዛሬ እጥረት እና በሀገሪቱ የሚወጡ አዳዲስ ህጎች የዘርፉ ተግዳሮቶች መሆናቸው ተጠቁሟል።
በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የአምራቾች በትበብር እና በቅንጅት መሥራት አስፈላጊ መሆኑን ኮማሪ ቢቨሬጅ ባዘጋጀው ፎረም አጽንኦት ተሰጥቶታል።
አዳዲስ ፈጠራዎችን በመሥራትና ዘመኑን የዋጁ ባለሞያዎችን በማሰልጠን የዘርፉን መጻኢ እድል ማጠናከር እንደሚገባም ተጠቅሷል።
በመጠጥ ዘርፍ የተሠማሩ አምራቾች በአካባቢ ጽዳትና በአየር ብክለት ሥራዎች ላይ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡም ተጠይቋል።
አምራቾቹ ከኢንዱስትሪዎቻቸው የሚወጡ ተረፈ ምርቶችን በአግባቡ በማስወገድ የአካባቢ ብክለትን መቅረፍ እንዳለባቸውም ተጠቁሟል።