የሀገር ውስጥ ዜና

ሕዝብን ያስቀደመ ስብዕና በመቅረጽ ሂደት የመምህራን ሚና የጎላ ነው – ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር)

By ዮሐንስ ደርበው

July 29, 2024

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ዜጋን ሙሉ ሰው በማድረግ ሀገርና ሕዝብን ያስቀደመ ስብዕና በመቅረጽ ሂደት የመምህራን ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስገነዘቡ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የክረምት ልዩ የመምህራን እና የትምህርት ቤት አመራሮች የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና መርሐ-ግብር መክፈቻን በበይነ-መረብ አስጀምረዋል፡፡

በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግርም የማትቆም ኢትዮጵያን ለመፍጠር መምህራን ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡

መምህራን በዘርፋቸው የሀገር ወታደሮች መሆናቸውን አስገንዝበው÷ ዜጋን ሙሉ ሰው አድርጎ ሀገርና ሕዝብን ያስቀደመ ስብዕና በመቅረጽ ሂደት የመምህራን ሚና ከፍተኛ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) በበኩላቸው 60 ሺህ መምህራንና የትምህርት ቤቶች አመራሮች በ28 ዩኒቨርሲቲዎች ስልጠና እንደሚወስዱ ገልጸው÷ ስልጠናው በልዩ ትኩረትና ክትትል እንደሚተገበር አስታውቀዋል፡፡

ስልጠናው የትምህርት ጥራትን እውን ለማድረግ ለተጀመረው ተግባር ግብዓት እንደሚሆንም አመላክተዋል፡፡

ከስልጠና በኋላ በሚሰጠው ፈተና ከ70 በመቶ በላይ የሚያመጡ መምህራን ከሌሎች አፈጻጸማቸው ጋር ተዳምሮ የዘላቂ አቅም የምስክር ወረቀትና የሥራ ደረጃን ከፍ ለማድረግ ግብዓት ይሆናል ብለዋል፡፡

በፍሬሕይወት ሰፊው