የሀገር ውስጥ ዜና

በትግራይ ክልል የሚደርሰው የሰብዓዊ መብት ጥሰት መቆም አለበት- አቶ ከበደ ጫኔ

By Tibebu Kebede

June 20, 2020

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የራያን ህዝብ የማንነት ጥያቄ ተከትሎ የትግራይ ክልላዊ መንግስት የሚያደርሰው የሰብዓዊ መብት ጥሰት መቆም እንዳለበት ተገለፀ።

ታጋይና የቀድሞው የብአዴን ኢህአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ ከበደ ጫኔ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ በራያ ህዝብ ላይ ለረዥም ጊዜ ሲደርስ የነበረው አፈናና ጭቆና አሁንም ቀጥሏል ብለዋል።

በኢትዮጵያ የራያን ህዝብ ጨምሮ የወልቃይትና ሌሎችም የማንነት ጥያቄዎች ሲነሱ መቆየታቸውን የገለፁት አቶ ከበደ ለህጋዊ ጥያቄ ህጋዊ መልስ እንጂ እስራት፣ ድብደባና ግድያ መልስ ሊሆን አይገባም ሲሉ ተናግረዋል።

የማንነት ጥያቄው በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ሲነሳ የነበረና እየተነሳ ያለ ቢሆንም በራያ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለው የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ አፈናና ጥሰት አሁንም ቀጥሏል ነው ያሉት።

የህይወት መጥፋት፣ አካል ማጉደል፣ ከመኖሪያ አካባቢያቸው የማፈናቀል ተግባር ህዝቡን በተወለደበት አካባቢ በነፃነት እንዳይኖር አድርጎታል ሲሉም ተናግረዋል።

“በህዝቡ ላይ እየደረሰ ያለው የህግ ጥሰት አግባብ አለመሆኑን ለምቀርባቸው የትግራይ አመራሮች ተናግሬ ነበር” የሚሉት አቶ ከበደ አመራሮቹ ድርጊቱን እንደሚያቆሙ ቢናገሩም በተግባር ግን የተቀየረ ነገር የለም ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የራያን ህዝብ የሌላ አካባቢ ተወላጅ እንዲያስተዳድረው በማድረግ የማንነት ጥያቄው እንዳይመለስና እንዲታፈን የማድረግ አዝማሚያዎችም ይታያሉ ሲሉ ተናግረዋል።

“የራያ ህዝብ የማንነት ጥያቄ መወሰን ያለበት በአማራ፣ በትግራይ ወይም በሌላ አካል አይደለም” የሚሉት አቶ ከበደ ይህን መወሰን የሚችለው የራያ ህዝብ ራሱ መሆኑን አስረድተዋል።

በመሆኑም የራያ ህዝብ የሚፈልገውን ውሳኔ የሚወስንበት ምቹ ሁኔታን ማመቻቸትና ህጋዊ መፍትሄ መስጠት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

የክልሉ መንግስት ህዝቡ የሚያነሳውን ጥያቄ እስከሚመለስለት ድረስ በነፃነት የሚኖርበትን ሁኔታ እንዲፈጥርም ጠይቀዋል።