የሀገር ውስጥ ዜና

በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩት የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንትን ጨምሮ 5 ሰዎች ፍርድ ቤት ቀረቡ

By Feven Bishaw

July 30, 2024

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በከባድ የሙስና ወንጀል የተጠረጠሩት የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ሀብታሙ አበበ (ዶ/ር) እና ምክትል ፕሬዚዳንት ታምራት ታገሰን (ዶ/ር) ጨምሮ አምስት ተጠርጣሪዎች ፍርድ ቤት ቀረቡ።

የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ላይ ተፈጽሟል በተባለ ምዝበራ የተጠረጠሩ የዩኒቨርሲቲ አመራሮች፣ ሰራተኞችና አንድ ኮንትራክተርን በሚመለከት የፌደራል ፖሊስ መርማሪ እና የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ ያቀረበውን የጊዜ ቀጠሮ መዝገብ የጥርጣሬ መነሻና የግራ ቀኝ ክርክር ተመልክቷል።

ተጠርጣሪዎቹ 1ኛ የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ሀብታሙ አበበ (ዶ/ር)፣ የዩኒቨርሲቲው አካዳሚና ምርምር ዘርፍ ምክትል ፕሬዚዳንት ታምራት ታገሰ (ዶ/ር)፣ 3ኛ የ1ኛ ተጠርጣሪ ባለቤትና ዩኒቨርሲቲው ጠቅላላ አገልግሎት ኃላፊ ወ/ሮ ደብሪቱ ተስፋዬ፣ 4ኛ ፀሐፊ የሆነችው የ3ኛ ተጠርጣሪ እህት ትዕግስት ተስፋዬ እና ኮንትራክተር የሆነው ደሳለኝ አስረዳ ናቸው።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ደቡብ ቅርጫፍ መርማሪና የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዐቃቤ ሕግ ስልጣንን ያለአግባብ መጠቀም ከባድ የሙስና ወንጀል መጠርጠራቸውን ጠቅሰው ለተጨማሪ ማጣሪያ የ14 ቀን ጊዜ ቀጠሮ ጠይቀዋል።

የተጠርጣሪ ጠበቆች ዐቃቤ ሕግ ምርመራ የመምራት ስልጣን እንዳለው ጠቅሰው፤ በጊዜ ቀጠሮ መዝገብ ላይ ግን ተሰይሞ የመከራከር ስነ ስርዓታዊ ስልጣን የለውም በማለት በችሎቱ ተሰይሞ ሊከራከር አይገባም ሲሉ ተቃውመዋል።

ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ ምርመራውን የመምራት የማገዝ እና በጊዜ ቀጠሮ መዝገቡ ተሰይሞ የመከራከር ስነ ስርዓታዊ መብት እንዳለው ጠቅሶ መልስ ሰጥቷል።

ፍርድ ቤቱም የዐቃቤ ሕግ ምርመራውን በመምራትና በመደገፍ በአዋጅ በተሰጠው ስልጣን ላይ ችሎት ተሰይሞ በጊዜ ቀጠሮ መዝገብ አይከራከር የሚል ስነ ስርዓታዊ ድንጋጌ እንደሌለ በመጥቀስ ዐቃቤ ሕግ እንዲሰየም ፈቅዷል።

በዚህም ዝርዝር የጥርጣሬ መነሻቸውን ዐቃቤ ሕግና መርማሪ ፖሊስ አቅርበዋል።

በተለይም የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ንግስት ኢሌኒ መታሰቢያ ሆስፒታል የኦክስጂን ማምረቻ ግንባታ ለማካሄድ መቀመጫውና ዋና መስሪያ ቤቱን ካናዳ ቶሮንቶ ካደረገ ለኤ.ኤ.ኤም.ኢዲ ቴክኖሎጂ ኢንካ የተባለ ድርጅት ጋር የመንግስት የግዢ መመሪያውን ባልጠበቀ መንገድ በአምስት አመት አፈጻጸሙ እየታየ መከፈል የሚገባውን በመተላለፍ አፈጻጸሙ ሳይታይ 57 ሚሊየን 383 ሺህ 956 ብር ከ72 ሳንቲም በመክፈል በመንግስት ላይ ጉዳት እንዲደርስ በማድረግ፤ በተጨማሪም ደሳለኝ አስረዳ የግንባታ ስራ ተቋራጭ ደግሞ የመምህራን መኖሪያ ቤት 2 ህንጻ ግንባታ ስራ በ2014 ዓ.ም ያልተገባ በተጋነነ ዋጋ 272 ሚሊየን 170 ሺህ 210 ብር ከ 60 ሳንቲም ክፍያ በመፈጸም በመንግስት ላይ ጉዳት በማድረስ እና ለውለታ 26 ሚሊዮን ብር ጥቅም ማስገኘትና ማግኘት የሚል የጥርጣሬ መነሻ ቀርቧል።

በተጨማሪም ለ3ኛ ተጠርጣሪ 42 ሺህ ብር እንዲሁም ለሌሎች ሁለት ሰራተኞች በተለያየ መጠን በአጠቃላይ 4 ሚሊዮን ብር በህገወጥ መንገድ የውሎ አበል ክፍያ እንዲፈጸም ተደርጓል የሚል የከባድ ሙስና የጥርጣሬ መነሻውን መርማሪና ዐቃቤ ሕግ በጋራ ለጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ አቅርበዋል።

ከ1ኛ እስከ 4ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ተጠርጣሪዎች ከዚህ በፊት በነበሩ ቀናቶች በሲዳማ ክልል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጊዜ ቀጠሮ ተጠይቆባቸው እንደነበር በመጥቀስ፣ በተሰጠ ጊዜ ቀጠሮ ውስጥ የተጠርጣሪዎችን የቃል መቀበል፣ አሻራ የማስነሳትና ሌሎች የምርመራ ስራዎችን ሲሰሩ እንደነበር ገልጸው፤ ተጠርጣሪዎቹ የተለያዩ ቦታዎች መኖራቸውን ተከትሎ ጉዳዩ በማዕከል እንዲታይ በተቋም በመወሰኑ መሰረት መዝገቡን ወደ ፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ማቅረባቸውን ገልጸዋል።

በምስክሮች ላይ በደረሰ ማስፈራሪያና ዛቻ ምክንያት ምስክሮችን ቃላቸውን ለመስጠት ስጋት እንዳደረባቸው ጠቅሰው የምስክሮችን ቃል አለመቀበላቸውን ለችሎት አብራርተዋል።

ከወንጀሉ ውስብስብነትና ከደረሰው ጉዳት አንጻር በተጀመረ ምርመራ ስራ ተጨማሪ ማስረጃ ለማሰባሰብና የምስክሮች ቃል ለመቀበል ተጨማሪ ጊዜ እንደሚያስፈልግ ፍርድ ቤቱ ተረድቶ በወ/መ/ስ/ህግ ቁጥር 59/1 መሰረት የ14 ቀን የምርመራ ማጣሪ ጊዜ ቀጠሮ ከ4ኛ ተጠርጣሪ ውጪ ባሉ ተጠርጣሪዎች ላይ እንዲፈቀድ መርማሪ ፖሊስና ዐቃቤ ሕግ ጠይቀዋል።

4ኛ ተጠርጣሪን በሚመለከት ካገኘችው 42 ሺህ ብር የውሎ አበል ጥቅም አንጻር ዋስትና ቢፈቀድላት እንደማይቃወም ዐቃቤ ሕግ ለችሎቱ ገልጿል።

ጠበቆች በበኩላቸው ተጠርጣሪዎች ላይ ከጥቅምት ወር 2016 ዓ.ም ጀምሮ ምርመራ ስራ ሲከናወን በነበረ ጊዜ ውስጥ ተጠርጣሪዎቹ በስራ ላይ ሆነው መርማሪን የመተባበር ስራ ሲያከናውኑ እንደነበር ጠቅሰው ምስክር አስፈራርተዋል ተብሎ መገለጹ ተገቢነት የሌለውና በማስረጃ የተደገፈ አይደለም በማለት ተከራክረዋል።

ሌላ ያልተያዘ ግብረአበር አለ በሚል ተጠርጣሪዎቹ በእስር ሊቆዩ እንደማይገባ እንዲሁም ቋሚ አድራሻ እንዳላቸው ጠቅሰው በመከራከር የዋስትና መብታቸው እዲፈቀድ ጠይቀዋል።

ግራ ቀኙን የተከታተለው ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ 3ኛ ተጠርጣሪ አገኘች ከተባለው ጥቅም አንጻር እንዲሁም ከአንድ አመት በታች የሆነ ህጻን ልጅ ይዛ የታሰረች በመሆኗ እና በዋስ ብትወጣ ማስረጃ የማጥፋት አቅም ሊኖራት አይችልም የሚለውን ግምት በመያዝ በ50 ሺህ ብር ዋስ እንድትወጣ የፈቀደ ሲሆን፤ 4ኛ ተጠርጣሪ በ10 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር እንድትፈታ ፈቅዷል።

ሌሎቹ ማለትም 1ኛ፣2ኛ እና 5ኛ ተጠርጣሪዎችን በሚመለከት ተጨማሪ ምርመራ ማጣሪያ እንዲደረግባቸው የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ ለፖሊስ ፈቅዷል።

በታሪክ አዱኛ