አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለማንኛውም ወርቅ አቅራቢ ክፍያ የሚፈጸመው የዕለቱን ዓለም አቀፍ የወርቅ ዋጋ በየዕለቱ ብሔራዊ ባንክ በሚያወጣው የውጭ ምንዛሪ ተመን ተባዝቶ እንደሚሆን ባንኩ አስታወቀ፡፡
ባንኩ የወርቅ መግዣ ዋጋን በሚመለከት ባወጣው መረጃ እንደገለጸው÷ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ወርቅን ከአምራቾችና አቅራቢዎች በብቸኝነት ይገዛል፡፡
የሚገዛበትንም ዋጋ በየጊዜው በመለዋወጥ አቅራቢዎችን ያበረታታል ነው የተባለው፡፡
በመሆኑም ባንኩ በውጭ ምንዛሬ ፖሊሲ ላይ ለውጥ በማድረግ በገበያ የሚመራ የፖሊሲ ማዕቀፍን ስለሚከተል ለማንኛውም ወርቅ አቅራቢ ክፍያ የሚፈጸመው የዕለቱን ዓለም ዓቀፍ የወርቅ ዋጋ ብሔራዊ ባንክ በየዕለቱ በሚያወጣው የውጭ ምንዛሪ ተመን ተባዝቶ እንደሚሆን ተገልጿል፡፡
ወርቅ አምራቾችና አቅራቢዎችም ይህንኑ አውቀው የዕለቱን የውጭ ምንዛሪ ተመን ከብሔራዊ ባንክ ድረ-ገጽ ላይ በማግኘት ለሚያቀርቡት ወርቅ ክፍያውን ወርቁን ከሸጡበት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፍ በየዕለቱ ማግኘት ይችላሉ ተብሏል፡፡