አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ፣ የኢትዮጵያና የአዲስ አበባ መግቢያ በር የሆነው የቦሌ መንገድ የኮሪደር ልማት ስራችን ከተማችንን በሚመጥን ገጽታ ዘመናዊ መሰረተ ልማቶችን አካቶ ሌላ ብስራት እና ተጨማሪ ድል ሆኖ ተጠናቋል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ÷ሰፊ የመኪና፣ የእግረኛ እና የብስክሌት መንገድ፣ የመኪና ማቆሚያ ፓርኪንጎች፣ የታክሲ እና አውቶቢስ መጫኛ እና ማውረጃዎች፣ የህዝብ መናፈሻዎች፣ አረንጓዴ ስፍራዎች ፣ ፋውንቴኖች፣ የህዝብ መጸዳጃ ስፍራዎች እንዲሁም የከተማችንን ፕላን የጠበቀ የቀለምና የመብራት ስራን አካትተን እጅግ በተዋበ መንገድ ገንብተን ለህዝብ አገልግሎት እነሆ ብለናል ሲሉ ገልጸዋል።
ይህ ስራ እንዲሳካ ከጅማሮው ከጎናችን የነበራችሁ አካላት በተለይም ህንጻችሁን ለእግረኞች እንዲሆን እና በተሰጣችሁ ዲዛይን በማደስ ከጎናችን የነበራችሁ የህንጻ ባለቤቶች፣ 24/7 ስራውን ያስተባበራችሁ በየደረጃው ያላችሁ የከተማችን አመራሮች፣ ኮንትራክተሮች፣ አማካሪዎች፣ የጉልበት ሰራተኞች እንዲሁም በመንገድ ስራው ምክንያት አመቺ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ባልነበረበት ወቅት በፍጹም ትዕግስት ስታበረታቱን ለነበራችሁ የከተማችን ነዋሪዎች ሁሉ ክብርና ምስጋና ላቀርብ እወዳለሁ ብለዋል።
እንዲህ ውብ ተደርጎ የተገነባውን መሰረተ ልማት መላው የከተማችን ነዋሪ ከጸጥታ አካላት ጋር በመሆን በባለቤትነት መንፈስ እንዲንከባከብ እና እንዲጠብቅ ጥሪዬን እያስተላለፍኩ አዲስን እንደ ስሟ ውብና አበባ ለማድረግ በላቀ ትጋትና ታማኝነት ማገልገላችንን እንቀጥላለን ሲሉም ከንቲባዋ አክለዋል::