አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢንዱስትሪ ፓርኮች የቻይና ባለሃብቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍስሃ ይታገሱ (ዶ/ር) ገለፁ።
በአዲስ አበባ እየተካሄደ ባለው አመታዊው የኢትዮ-ቻይና ቢዝነስ ፎረም ላይ ዋና ስራ አስፈፃሚው እንደገለጹት÷ በኢትዮጵያ በሚገኙ የኢንዱስትሪ ፓርኮች እና የነፃ የንግድ ቀጠና የቻይና ባለሃብቶች ተሳትፎ ከፍተኛ ነው፡፡
የባለሀብቶቹን ተሳትፎ ይበልጥ ለማጠናከር የሚያስችሉ ተቋማዊ ሪፎርም ተግባራዊ መደረጋቸውንም ጠቅሰዋል፡፡
የኢትዮ-ቻይና ቢዝነስ ፎረም ኢትዮጵያ እና ቻይና በንግድ እና ኢንቨስትመንት መስክ ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር ያለመ ፎረም ነው፡፡
በፎረሙ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች እና የንግዱ ማህበረሰብ አባላት እንዲሁም ከተለያዩ የቻይና ግዛቶች የተውጣጡ ከፍተኛ የመንግስት እና የቢዝነስ ተቋማት ልዑካን እየተሳተፉ እንደሚገኙ ተመላክቷል፡፡
ከ90 በላይ የቻይና ባለሀብቶችን የያዘዉ ልዑካን ቡድን በነገዉ እለት በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ የመስክ ጉብኝት ያደርጋል መባሉን ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡