አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአውሮፓ ሕብረት ዘጠኝ ተሽከርካሪዎችን ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስረክቧል፡፡
የአውሮፓ ሕብረት በኢትዮጵያ የወንጀል ፍትሕ አስተዳደርን ለመደገፍ በሚደረገው እንቅስቃሴ የተለያዩ የድጋፎች ማዕቀፎችን የያዘ ፕሮጀክት ቀርፆ በትግባራ ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡
በኢትዮጵያ የአውሮፓ ሕብረት አምባሳደር ሮናልድ ኮቢያ ለመስክ ሥራ አገልግሎት የሚውሉ ተሽከርካሪዎችን ለፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት ቴዎድሮስ ምህረት አስረክበዋል፡፡
አቶ ቴዎድሮስ ምህረት በዚሁ ወቅት ÷ የአውሮፓ ሕብረት በፍርድ ቤቱ የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ሪፎርም ላይ የሚያደርገው ድጋፍ የዳኝነት ስርዓቱ ላይ ደጋፊ ሚና እንዳለው በመግለጽ አመስግነዋል፡፡
አምባሳደር ሮናልድ ኮቢያ በበኩላቸው በአውሮፓ ሕብረት ለፍርድ ቤቱ የተደረገው የተሽከርካሪ ድጋፍ ከታቀደው አንፃር አነስተኛ መሆኑን ገልጸው ፥ የፍትሕ ዘርፉን ለመደገፍና ለማጠናከር ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
የርክክብ ሥነ-ስርዓት ከተከናወነ በኋላ ፍርድ ቤቱ በቅርቡ ያስገነባውንና የዳኝነት አገልግሎቱን በቴክኖሎጂ በታገዘ ሁኔታ ለመስጠት የሚያስችለውን ስማርት ኮርት ሩም የሥራ ሃላፊዎቹ መጎብኘታውን የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡