የሀገር ውስጥ ዜና

አምባሳደሮች ኃላፊነታቸውን በትጋት እንዲወጡ ተጠየቀ

By ዮሐንስ ደርበው

August 02, 2024

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 26፣ 2016(ኤፍ ቢ ሲ) አዲስ የተሾሙ አምባሳደሮች የተጣለባቸውን ኃላፊነት በትጋት መወጣት እንደሚጠበቅባቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አሳሰበ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብዩ ተድላ በሰጡት መግለጫ÷ ሀገርን መወከል ትልቅ ክብር መሆኑን በመግለፅ አዲስ ተሿሚ አምባሳደሮች የተጣለባቸውን ኃላፊነት በትጋት መወጣት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል፡፡

ያላቸውን ልምድ በመጠቀም ተለዋዋጩን የዓለም አቀፍ ሁኔታ ተረድተው በዲፕሎማሲው መስክ ለሀገራቸው ጥቅም በትጋት እንዲሠሩም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አሳስቧል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የሥራ ስምሪት ስምምነት ባልፈጸመችባቸው አንዳንድ የእስያ ሀገራት በሕገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች አማካኝነት እየተደረገ ያለ እንቅስቃሴ መኖሩን በመጠቆም ሕብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ መክረዋል፡፡

ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ሀገራት ጋር በችግር ውስጥ ያሉ ዜጎችን ለመመለስ እና ይህን ሕገ-ወጥ ድርጊት ለማስቆም መንግሥት እሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡