አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በዘንድሮ ኦሊምፒክ ድል ያስመዘግባሉ ተብለው ግምት ከተሰጣቸው መካከል አትሌት ሻ ካሪ ሪቻርድሰን አንዷ ናት።
በፈረንሳይ ፓሪስ እየተካሄደ በሚገኘው የ33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ውድድር ከፍተኛ የማሸነፍ ግምት የተሰጣት አሜሪካዊቷ አትሌት ሻ ካሪ ሪቻርድሰን ማጣሪያውን አስገራሚ ብቃት በማሳየት በቀዳሚነት አጠናቃለች።
የ24 ዓመቷ አትሌት ዛሬ በተደረገው የ100 ሜትር የሴቶች ማጣሪያ ውድድር በ10 ሴኮንድ ከ94 ማይክሮ ሴኮንድ በመግባት ወደ ቀጣዩ ዙር አልፋለች፡፡
አትሌቷ ማሪዋና የተባለው የአበረታች ዕፅ በሰውነቷን መገኘቱን ተከትሎ ከዚህ ቀደም በተካሄደው የቶኪዮ ኦሊምፒክ ሳትሳተፍ መቅረቷ ይታወሳል፡፡
በዓለም አቀፉ የፀረ አበረታች መድሀኒቶች ኤጀንሲ ከተጣለባት እገዳ በኋላ ወደ ውድድር የተመለሰችው ሪቻርድሰን በ2023ቱ የዓለም ሻምፒዮና አስደናቂ ብቃቷን በማሳየት የወርቅ ሜዳሊያ አሸንፋለች፡፡
በቡዳፔስቱ የዓለም ሻምፒዮና ተቸግራ ለፍፃሜ ያለፈችው ሪቻርድሰን በፍፃሜው ጃማይካዊቷን አትሌት ሼሪካ ጃክሰን እና የ5 ጊዜ የዓለም ሻምፒዮኗን ሼሊ አን ፈሬዘር በማሸነፍ የወርቅ ባለቤት መሆኗ ሚታወስ ነው፡፡
የፕላኔታችን ፈጣኗ ሴት አትሌት ፍጥነቷን ለማሳየት ከምትጥረው በላይ ከልክ ያለፈ የአሸናፊነቷን ስሜት በመግለፅ ላይ ታተኩራች በሚል ከስፖርት ቤተሰቡ ትችት የሚቀርብባት ሲሆን ከብዙ መሰናክሎች በኋላ አሁንም በአይበገሬነቷ ለብዙ ስፖርተኞች ተምሳሌት ናት፡፡
በረዣዥም ልጥፍ ጥፍሮቿ እና በባለ ደማቅ ቀለም ዊጎቿ የምትታወቀው ተስፈንጣሪዋ አትሌት በ2023ቱ የዓለም ሻምፒዮና 10 ሴኮንድ ከ64 ማይክሮ ሴኮንድ በመግባት የምንጊዜም የሴቶች 100 ሜትር ፈጣን ሰዓት ባለቤት ናት፡፡
በዛሬው እለት በስታድ ዲ ፍራንስ በቀላሉ ወደ ቀጣዩ ዙር ያለፈችው አነጋጋሪዋ አትሌት በመጪው ቅዳሜ የ100 ሜትር የግማሽ ፍፃሜ ውድድሯን የምታደርግ መሆኑን የዓለም አትሌቲክስ አስነብቧል፡፡