የሀገር ውስጥ ዜና

በአለርት ሆስፒታል የሕክምና መሳሪያዎች የሚታደሱበት ማዕከል ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ 

By Mikias Ayele

August 05, 2024

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአለርት ኮምፕሬንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሕክምና መሳሪያዎች የሚታደሱበት ማዕከል ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ።

የመሰረት ድንጋዩን የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ እና በኢትዮጵያ የኮሪያ ሪፐብሊክ አምባሳደር ጁንግ ካንግ አስቀምጠዋል።

ዶ/ር መቅደስ ዳባ÷ እንደ ሀገር ያረጁ የሕክምና ግብዓቶችን መልሶ በመጠቀም ረገድ ክፍተቶች መኖራቸውን ተናግረዋል።

በዚህም ምክንያት በርካታ የሕክምና መሣሪያዎች ታድሰው ዳግም አገልግሎት መስጠት እየቻሉ ለብክነት ይዳረጉ እንደነበር አስታውሰዋል።

ዛሬ ግንባታው የተጀመረው ማዕከል ያረጁ የሕክምና መሳሪያዎችን አያያዝና አጠቃቀም የሚያሻሽል መሆኑንም ገልጸዋል።

ግንባታው በኮሪያው ሪፐብሊክ ዓለም አቀፍ የጤና እንክብካቤ ፋውንዴሽን(ኮፊ) በተደረገ የገንዘብ ድጋፍ የሚካሄድ መሆኑን ጠቁመው ÷በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት እንደሚበቃ ተናግረዋል።

ማዕከሉ ከኢትዮጵያ ባለፈ ለጎረቤት ሀገራት ጭምር አገልግሎት እንዲሰጥ ታስቦ እንደሚገነባ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

አምባሳደር ጁንግ ካንግ በበኩላቸው÷ ኮሪያ ሪፐብሊክና ኢትዮጵያ የጋራ ተጠቃሚነት ላይ መሰረት ያደረገ ጠንካራ ወዳጅነት ያላቸው ሀገራት ናቸው ብለዋል።

ሁለቱ ሀገራት በተለያዩ የልማት መስኮች ላይ በትብብር እየሰሩ መሆኑንም አምባሳደሩ ገልጸዋል።

ዛሬ የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠለት ማዕከል በኢትዮጵያ የሕክምና መሳሪያዎችን በማደስና ወደ ሥራ በማስገባት የሀገሪቱን የጤና አገልግሎት ለማሻሻል ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ተናግረዋል።