የሀገር ውስጥ ዜና

የዳያስፖራ አደረጃጀቶች የሁሉም ድምጽ በእኩልነት የሚሰማባቸው ሊሆኑ ይገባል – አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ

By Shambel Mihret

August 06, 2024

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የዳያስፖራ አደረጃጀቶች ኢትዮጵያን የሚመስሉና የሁሉም ድምጽ በእኩልነት የሚሰማባቸው ሊሆኑ እንደሚገባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ገለጹ።

ሚኒስትር ዴኤታው በሰሜን አሜሪካ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ካቀፈው ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ለብልጽግና እና ለብዝኃነት የልዑካን ቡድን አባላት ጋር ትውውቅና ውይይት አካሂደዋል፡፡

አምባሳደር ምስጋኑ በዚሁ ወቅት÷ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ በልዩ ልዩ መስኮች የሚያደርጉት አስተዋጽኦ የሚበረታታ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ዳያስፖራው ባደገ ሀገር፣ ባህልና ዴሞክራሲ ውስጥ የሚኖር እንደመሆኑ መጠን በዚሁ ልክ ለማደግና ለመበልጸግ ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

እንዲሁም የሁሉም ድምጽ በእኩል የሚሰማበትና ኢትዮጵያን የመሰለ ጠንካራ አደረጃጀት እንዲፈጥሩም መግለጻቸውን ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

አደረጃጀቶችን በመጠቀምም በውጭ ሀገራት ተወልደው ያደጉ ሁለተኛና ቀጣይ ትውልዶችን ስለሀገራቸውና ማንነታቸው ግንዛቤ እንዲኖራቸው እንዲያደርጉና በሀገር ቤት የሚከናወኑ የልማት ስራዎችን እንዲያስተዋውቁም ጠይቀዋል።