የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያና ደቡብ ኮሪያ ወታደራዊ ግንኙነታቸው ተጠናክሮ ይቀጥላል – አይሻ መሐመድ (ኢ/ር)

By Shambel Mihret

August 06, 2024

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለረጅም ዘመን የዘለቀው የኢትዮጵያ እና የደቡብ ኮሪያ ወታደራዊ ግንኙነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሐመድ (ኢ/ር) ገለፁ፡፡

አይሻ መሐመድ (ኢ/ር) በደቡብ ኮሪያ የቀድሞ ዘማቾች ጉዳይ ሚኒስትር ካንግ ጁንግ-አይ ከተመራ ልዑካን ቡድን ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይቱ የሁለቱ ሀገራት ታሪካዊ ግንኙነት ዘመን ያስቆጠረ እንደሆነና ታሪካዊ ግንኙነቱንም ሊያጠናክሩ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ አብሮ ለመስራት ፅኑ ፍላጎት እንዳለ ተገልጿል፡፡

አይሻ መሐመድ (ኢ/ር) በዚሁ ወቅት÷ የኢትዮጵያ ወታደር በኮሪያ የሰላም ማስከበር ግዳጅ በተሰማራበት ወቅት የፈፀመው ወታደራዊ ጀብዱ እና የሰንደቅ-ዓላማ ፍቅር እስካሁን ድረስ ሁለቱ ሀገራት የሚኮሩበት ድንቅ ተግባር መሆኑን አስታውሰዋል፡፡

ታሪኩን በሚያከብር መልኩም ለረጅም ጊዜ የዘለቀውን የሁለቱን ሀገራት ወታደራዊ ግንኙነት የበለጠ አጠናክሮ ማስቀጠል ተገቢ መሆኑንም መናገራቸውን የመከላከያ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መረጃ አመላክቷል።

በኢትዮጵያ የደቡብ ኮሪያ ወታደራዊ አታሼ ቢሮ የደቡብ ኮሪያ የቀድሞ ዘማቾች ጉዳይ ሚኒስትር ካንግ ጁንግ-አይ በበኩላቸው÷ የሀገራቱ ወዳጅነትና ታሪካዊ ትስስር አሁን ላለው ትውልድ ብቻ ሳይሆን ለቀጣይ ትውልድም መሻገር ያለበት በመሆኑ የጋራ ታሪኩ ተሰንዶ ሊቀመጥ ይገባል ብለዋል፡፡