የሀገር ውስጥ ዜና

ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀንን አስመልክቶ የፓናል ውይይት እየተካሄደ ነው

By Feven Bishaw

August 08, 2024

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ24ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ21ኛ ጊዜ የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀንን አስመልክቶ ፓናል ውይይት እየተካሄደ ነው።

በሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አዘጋጅነት እየተካሄደ የሚገኘው የፖናል ውይይት “ወጣቶችን በቴክኖሎጂ ማብቃት ለዘላቂ ልማት ግቦች” በሚል መሪ ሀሳብ ነሐሴ 6 ቀን 2016 ዓ.ም የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀንን አስመልክቶ የተዘጋጀ ነው።

በመድረኩ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ሙና አህመድ÷ ቀኑን በዚህ መሪ ሃሳብ ማክበር ያስፈለገበት ምክንያት የዲጂታል ቴክኖሎጂው ለዘላቂ ልማት ባለው ከፍተኛ ድርሻ መሆኑን ገልጸዋል።

ዘርፉ የዓለምን የወደፊት ሁኔታን እንደሚቀርጽ ጠቅሰው፤ ወጣቶች እንዲጠቀሙ በማስቻል ረገድ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ መሆኑን አመላክተዋል።

በመድረኩ ከተለያዩ ተቋማት የተወጣጡ የስራ ሀላፊዎች እንዲሁም ከተለያዩ ወጣት አደረጃጀቶች የተወጣጡ ወጣቶች እየተሳተፉ ነው።

በትዝታ ደሳለኝ