የሀገር ውስጥ ዜና

የአምራች ኢንዱስትሪ ፖሊሲን ተግባራዊ ለማድረግ የግሉ ዘርፍ ሚና የጎላ መሆኑ ተገለጸ

By Shambel Mihret

August 08, 2024

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ጋር ለመስራት የሚያስችል ውይይት አካሂዷል፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል በመድረኩ÷ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍን ለማሳደግ ወደ ስራ የገባውን አዲሱን የአምራች ኢንዱስትሪ ፖሊሲ ተግባራዊ ለማድረግ የግሉ ዘርፍ ሚና የጎላ መሆኑን ገልፀዋል።

ዘመናዊና ተወዳዳሪ የሆነውን ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በመጠቀም የፖሊሲ ማስፈፀሚያ ለማድረግ በጋራ መስራት ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡

በተለይም በተኪ ምርት፣ የምርት አቅም አጠቃቀም እና እሴት በመጨመር የወጪ ንግድ በማሳደግ ላይ ትኩረት በማድረግ በጋራ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

የገበያ ጉድለት በመንግስት አቅም ብቻ የማይሞላ በመሆኑ ሚድሮክ በተጠናከረ መንገድ ገበያውን ለመሙላት መስራት እንዳለበትም ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡

በተለይም በሀገር ውስጥ ተመርተው ለሌሎች አምራች ኢንዱስትሪዎች ግብዓት የሚሆኑ ምርቶች ላይ ትኩረት በማድረግ ሜጋ ፕሮጀክቶችን ኢንዲሰራ በቀጣይ ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡

የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ጀማል አህመድ በበኩላቸው÷ በስሩ ያሉ ድርጅቶችን ከኪሳራ በማዳን የምርት ጥራታቸውን በማሳደግ ሰርቲፋይድ የማድረግ ስራዎች መሰራታቸውን ገልፀዋል፡፡

የአምራች ኢንዱስትሪውን ዘርፍ ለማሳደግ ከመንግስት ተቋማት ጋር ተቀራርቦ ለመስራት ሚድሮክ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለውም መግለጻቸውን ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

የሀገር ውስጥ ምርቶች ተወዳዳሪነታቸው እንዲያድግ በዘርፉ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ከመንግስት ጋር ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡