አዲስ አበባ፣ ሰኔ 15፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የዚምባብዌ የፀረ ሙስና ኮሚሽን በሃገሪቱ ሃብታሞች የገንዘብ ምንጭ ላይ ምርመራ ጀመረ።
ምርመራው በሃገሪቱ ባለ ጸጎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግ የሃብት ምንጫቸውን ማጣራትና እነርሱ የሚያንቀሳቅሱት ድርጅት ግብር መክፈል አለመክፈሉን የሚያካትት መሆኑን የፀረ ሙስና ኮሚሽነሩ ማታንዳ ሞዮ ተናግረዋል።
በዚህ ሂደት መሰረትም ባለ ጸጎቹ የሃብት ምንጫቸውን በሃገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀርበው አሳማኝ በሆነ መልኩ ማስረዳት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።
ይህ ሳይሆን ቢቀርና የሃብት ምንጫቸውን በአግባቡ ማስረዳት ካልቻሉ ግን ያካበቱት ሃብት በመንግስት ይወረሳል ነው የተባለው።
ባለሃብቶቹ ከፍርድ ቤት ከሙስና ነጻ ናቸው የሚል ማስረጃ ቢያገኙም እንኳን የገንዘብ ምንጫቸውን አሳማኝ በሆነ መልኩ ካላስረዱና ማስረጃ ካላቀረቡ ሃብት ንብረታቸው ይወረሳልም ተብሏል።
የሃገሪቱ ፀረ ሙስና ኮሚሽን ባለፈው የፈረንጆቹ አመት ሃምሌ ወር ላይ ይህን የሃብት ምንጭ የማጣራት ሂደት እንዲያከናውን ስልጣን ተሰጥቶታል።
ሃገሪቱ ለአመታት በከፋ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ውስጥ ትገኛለች።
የሃገሬው ዜጎችም ሙስና እና የተበላሸ አሰራር ባስከተለው የኑሮ ጫና ምክንያት ተቃውሞ እያሰሙ ነው።
በሃገሪቱ ለኮሮና ቫይረስ በሚል የተካሄደው የመድሃኒትና ቁሳቁስ ግዢም ለሙስና የተጋለጠ ነበር ተብሏል።
ከዚህ ጋር ተያይዞም የሃገሪቱ ጤና ሚኒስትር ኦባዲያህ ሞዮም ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ክስ ቀርቦባቸዋል።
በዚምባብዌ 63 በመቶው የሃገሬው ዜጎች ከድህነት ወለል በታች ሲገኙ 23 በመቶ ህጻናት ደግሞ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ካስቀመጠው የህጻናት እድገት መለኪያ በታች መሆናቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ።
ምንጭ፡- ቢቢሲ