የሀገር ውስጥ ዜና

ፎረሙ ባለሃብቶች በግብርና ላይ ግንዛቤ አግኝተው እንዲሠሩ ያግዛል- ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)

By Shambel Mihret

August 13, 2024

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ብሔራዊ የግብርና ኢንቨስትመንት ፎረም በግብርና ሜካናይዜሽን፣ በመስኖ ስንዴ ልማት፣ በአፈር ጤና፣ በእንስሳት መኖ ልማት እና በእንስሳት ልማት ላይ ባለሀብቶች በቂ ግንዛቤ አግኝተው እንዲሠሩ ያግዛል ተባለ፡፡

“የግብርናውን ዘርፍ እምቅ አቅም እንጠቀም” በሚል መሪ ሐሳብ ከነገ ጀምሮ የሚካሄደውን ብሔራዊ የግብርና ኢንቨስትመንት ፎረም ምክንያት በማድረግ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር ) ከዓለም የምግብ እና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) ልዑክ ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም በአረንጓዴ ዐሻራ፣ በመስኖ ስንዴ ልማት እና በሌማት ትሩፋት በተገኙት ምርጥ ተሞክሮዎች በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ከኢትዮጵያ ልምድ መቅሰማቸውን ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡

የፋኦ ዋና የኢኮኖሚ አማካሪ ማክሲሞ ቶሬሮ (ዶ/ር) በበኩላቸው ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ያስመዘገበችው ውጤት ለአፍሪካ ሀገራት ምሳሌ ነው፤ የተቋማችን ድጋፍም ተጠናክሮ ይቀጥላል ማለታቸውን የግብርና ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡