አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 15፣ 2016 ዓ.ም (ኤፍ ቢ ሲ) በቡድን ተደራጅተው የሕዝቡን ሰላም የሚያውኩ የሽብር እና ፅንፈኛ ቡድኖችን ለመቆጣጠር በቅንጅት መሥራት እንደሚገባ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል አሳሰቡ፡፡
የ2017 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከፍተኛ አመራሮች፣ የክልልና የከተማ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽነሮች በሀገራዊ የፖሊስ የፀጥታ ዕቅድ ላይ ተወያይተዋል።
በውይይቱም ሀገራዊ ፀጥታን ለማስፈን በወንጀል መከላከል እና በወንጀል ምርመራ መከናወን ያለባቸው አንኳር ጉዳዮች ተነስተዋል፡፡
በዚህም የፖሊስ ሪፎርም በተሟላ መልኩ እንደሀገር እየተተገበረ መሆኑ የተገመገመ ሲሆን÷ በቀጣይም የሠራዊቱን አቅም በሁለንተናዊ መልኩ ለመገንባት እና ፖሊስ ከኅብረተሰቡ ጋር ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ከሕዝቡ ጋር የበለጠ ተቀራርቦ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት መሠራት አለበት ተብሏል፡፡
ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ በውይይቱ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ በ2016 በጀት ዓመት ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፈን በሀገራችን የተሻለ ሰላም እንዲረጋገጥ፤ ፖሊስ እንደ አንድ የፀጥታ ተቋም ተቀናጅቶ እየሰራ መሆኑንና በቀጣይም ይህንኑ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል፡፡
በ2017 ዓ.ም የፌደራል፣ የክልልና የከተማ አስተዳደር ፖሊስ ተቋማት በሀገራችን የሚካሄዱ ሕዝባዊና መንግስታዊ ሁነቶች በሰላም እንዲጠናቀቁ ከወዲሁ አስፈላጊውን ዝግጅት እንዲደረግ አመላክተዋል፡፡
በቡድን ተደራጅተው የሕዝቡን ሰላም የሚያውኩ የሽብር እና ፅንፈኛ ቡድኖችን ለመቆጣጠርም በቅንጅት መስራት ይገባል ነው ያሉት፡፡