የሀገር ውስጥ ዜና

280 ሺህ ዶላር ደብቆ ሲንቀሳቀስ በቁጥጥር ሥር የዋለው ተጠርጣሪ ክስ ተመሰረተበት

By ዮሐንስ ደርበው

August 22, 2024

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) 280 ሺህ የአሜሪካ ዶላር በመኪና አካል ውስጥ በመደበቅ ሲንቀሳቀስ በቁጥጥር ሥር የዋለው ተጠርጣሪ ክስ ተመሰረተበት።

ተከሳሽ ሾፌር ኢንድሪስ ይማም በአፋር ክልል አፋምቦ ወረዳ አሳይታ አካባቢ ነዋሪ ነው።

የኦሮሚያ ክልል ፍትሕ ቢሮ ምሥራቅ ሸዋ ዞን ምድብ ዐቃቤ ሕግ የብሔራዊ ባንክ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 591/2000 አንቀጽ 26 ሥር የተመላከተውን ድንጋጌ ጠቅሶ በተጠርጣሪው ላይ ዝርዝር ክስ አቅርቧል፡፡

ተከሳሹ ግንቦት 22 ቀን 2016 የሰሌዳ ቁጥሩ አ አ የሆነ ሱዙኪ የቤት መኪና ይዞ ከአዳማ ተነስቶ ወደ ሐረር እየተጎዘ ሳለ ፈንታሌ ወረዳ ኬላ አካባቢ በኬላ ተቆጣጣሪዎችና በፀጥታ አካላት ሲፈተሽ በመኪናው አካል ውስጥ 280 ሺህ የአሜሪካ ዶላር በወቅቱ በነበረ ምንዛሬ 15 ሚሊየን 994 ሺህ 888 ብር ደብቆ መያዙ በክሱ ተመላክቷል፡፡

በዚህም በሕግ ከተፈቀደው መጠን በላይ የአሜሪካ ዶላር ይዞ መገኘት ወንጀል ክስ የቀረበበት ሲሆን÷ በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተረኛ ወንጀል ችሎት ቀርቦ የክስ ዝርዝሩ ደርሶታል፡፡

ፍርድ ቤቱም ተከሳሹ ከጠበቃው ጋር ተማክሮ እንዲቀርብ ለነሐሴ 21 ቀን 2016 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

በታሪክ አዱኛ