የሀገር ውስጥ ዜና

የኦሮሚያ ክልል ለ3 ሺህ 611 ታራሚዎች ይቅርታ አደረገ

By Melaku Gedif

August 28, 2024

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል ለ3 ሺህ 611 ታራሚዎች ይቅርታ መደረጉን የክልሉ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ቢሮ አስታውቋል፡፡

የቢሮው ሃላፊ ጉዮ ዋሪዮ በሰጡት መግለጫ÷በይቅርታ ከተፈቱት ውስጥ 247ቱ ሴቶች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ይቅርታ የተደረገላቸው የሕግ ታራሚዎች በማረሚያ ቤት ቆይታቸው መልካም ባህሪ ማሳየታቸውና ከቅጣቱ መማራቸው በሚመለከተው አካል የተረጋገጠ መሆኑን አንስተዋል።

ታዳጊ ታራሚዎች ሆነው አንድ አራተኛ የእስር ጊዜያቸውን ያጠናቀቁ እንዲሁም ልጅ ይዘው በማረሚያ ቤት የሚገኙና ነፍሰ ጡሮች ይቅርታ ከተደረገላቸው መካከል መሆናቸውንም አመልክተዋል፡፡

በተጨማሪም እድሜያቸው ከ60 ዓመት በላይ የሆኑ አዛውንቶችና የዕድሜ ልክ እስራት ተፈርዶባቸው ከ10 ዓመት በላይ በማረሚያ ቤት ያሳለፉ ይቅርታ እንደተደረገላቸው ተናግረዋል።

በግማዊ ዴክሲሳ