የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ ሴሚናር በዘላቂ ልማት ግቦች ስኬት ያላትን ተሞክሮ አካፈለች

By Melaku Gedif

August 29, 2024

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በቻይና ቤጂንግ በተካሄደው ዓለም አቀፍ ሴሚናር ላይ በዘላቂ ልማት ግቦች ስኬት ዙሪያ ያላትን ተሞክሮ ለሌሎች ማካፈሏን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታውቋል፡፡

የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ቤልጅጌ (ዶ/ር) በዘላቂ የልማት ግቦች አፈጻጸም በሕግ አውጪው ወይም በፓርላማ ሚና ዙሪያ የኢትዮጵያን ልምድ አቅርበዋል።

በዘላቂ ልማት ግቦች ስኬት ዙሪያ ባተኮረው ዓለም አቀፍ ሴሚናር ላይ ኢትዮጵያ ተሞክሮዋን ለሌሎች ማካፈሏንና ልምድ መቅሰሟንም ተናግረዋል፡፡

በቻይና በተለያዩ ዘርፎች እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ሥራዎች በእርግጥም ቻይና የዓለም ግዙፍ ኢኮኖሚን መገንባት መቻሏን ማሳያ ምስክሮች ናቸው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያም ከቻይና ልምድ በመውሰድ አሁን የጀመረችውን አመርቂ የለውጥ ጉዞ በማፋጠን ሕዝቦቿን ወደ ብልጽግና ማሸጋገር እንደምትችል ጥሩ ማሳያ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ለዚህም በኢትዮጵያ እየተከናወኑ የሚገኙ የአዲስ አበባና ሌሎች ከተሞች የኮሪደር ልማት፣ የገጠርና የከተማ ግብርና፣ የቱሪዝም መዳረሻዎችና የወንዝ ዳር ፕሮጀክቶችን ጠቅሰዋል።

እነዚህ የዓለምን ደረጃ የጠበቁና ተወዳዳሪ የሆኑ ሥራዎች ከመሆናቸው ባሻገር ኢትዮጵያ በትክክለኛ የልማት ጎዳና ላይ ያለችና ለሌሎች ሀገራትም አርአያ መሆን እንደምትችል ያሳዩ ናቸው ማለታቸውን የም/ቤቱ መረጃ ያመላክታል፡፡