የሀገር ውስጥ ዜና

ብሔራዊ የሲቪል አቪዬሽን ትራንስፎርሜሽን መርሐ-ግብር ይፋ ሆነ

By ዮሐንስ ደርበው

September 03, 2024

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን በአቪዬሽን መስክ ኢትዮጵያን ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግራትን ብሔራዊ የሲቪል አቪዬሽን ትራንስፎርሜሽን መርሐ-ግብር ይፋ አደረገ፡፡

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴዔታ ዳንጌ ቦሩ እንደገለጹት÷ ኢትዮጵያ በአፍሪካ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ መሪነቷን በዘላቂነት ለማስቀጠል ሁሉን አቀፍ ለሆነ የዘርፉ መዘመን ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ነው።

መርሐ-ግብሩ ዘርፉን በላቀ ቴክኖሎጂ የማስቀጠል ትልም እንዳለው ገልጸው÷ በመጪው ጊዜም ቴክኖሎጂን ማዕከል ያደረገ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ደኅንነትን የማስጠበቅ ሥራ ይቀጥላል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ጌታቸው መንግሥቴ በበኩላቸው÷ መርሐ-ግብሩ ኢትዮጵያ በአቪዬሽን ዘርፍ ደኅንነት የላቀ ተግባር ለማከናወን ቁርጠኛ መሆኗን የሚያመላክት ነው ብለዋል።

ይህ ትራንስፎርሜሽን እያደገ የመጣውን የአቪዬሽን መስክ መሰረት በማድረግ ዘርፉ የሚጠይቀውን አሁናዊ ቁመና ለመላበስ የሚያስችል መሆኑንም አመላክተዋል፡፡