የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያስችሉ የህክምና ቁሳቁሶች ድጋፍን ለጅቡቲ አደረገች

By Meseret Demissu

June 25, 2020

አዲስ አበባ ፣ሰኔ 18 ፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያ የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከልና ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ የህክምና ቁሳቁሶች ድጋፍን ለጅቡቲ አደረገች።

ኢትዮጵያ የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከልና በሽታው ከተከሰተ በኋላም ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ ግምቱ ከ300 ሺህ የአሜሪካን ዶላር በላይ ዋጋ ያለው ልዩ ልዩ የህክምና መስጫ መድሀኒቶችንና ቁሳቁሶችን  ዛሬ ለጅቡቲ ዕርዳታ ሰጥታለች ፡፡

እርዳታውን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ዛሬ ጅቡቲ በመገኘት አስረክበዋል፡፡

አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን  በርክክብ ሥነ-ስርዓቱ ላይ ÷ሁለቱ አገራት ስትራቴጂያዊ አጋርነት በመልካም ጊዜ ብቻ ሳይሆን እንደ ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በሚከሰትባቸው አስከፊ ወቅቶችም በጋራ የሚቆሙ መሆናቸውንና የዛሬው ድጋፍም የዚሁ ማሳያ መሆኑን  አንስተዋል፡፡

ሁለቱ አገራት የጋራ ድንበር የሚጋሩ ከመሆናቸው አንጸር በሽታውን ለመከላከል በጋራ ተባብረው መስራት ይገባቸዋል ብለዋል።

ከዚያም ባለፈ በቀጣይም በጤናና ሌሎች ዘርፎች የሁለትዮሽ ትብብራቸውን ማጠናከር እንደሚገባቸው ገልጸዋል፡፡

በተያያዘ ዜና አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ከጅቡቲ የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር መሀመድ የሱፍ ጋር በሁለትዮሽ ግንኙነት አካባቢያዊ እና ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡

በወቅቱም አምባሳደር ሬድዋን ሁለቱ አገራት የጋራ ባህል፣ ቋንቋ እና ታሪካዊ ዳራ የሚጋሩና ስትራቴጂክ አጋር መሆናቸውን ጠቅሰው በሁሉም መስኮች ያሉትን የሁለቱን አገራት ግንኙነቶች አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ አንስተዋል፡፡

አያይዘውም የሁለትዮሽ ግንኙነቱን የበለጠ ለማጠናከር በኢትዮጵያ በኩል ያለውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል፡፡

የጅቡቲ የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ሙሀመድ የሱፍ በበኩላቸው ÷ኢትዮጵያ በዕርዳታ መልክ ላቀረበቻቸው የህክምና ግብዓቶች በጅቡቲ መንግስትና ህዝብ ስም የላቀ ምስጋናቸውን በማቅረብ ይህ ዓይነቱ ተግባር የሁለቱን አገራት ጥብቅ ወዳጅነት ማሳያ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም ጅበቲ እንደቀድሞ ሁሉ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም እንደምታከብርና በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይም ከጎኗ እንደምትቆም አረጋግጠዋል፡፡

በቀጣይም ሁለቱ አገራት በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት መስኮች ያሉትን ትብብሮች ይበልጥ ለማጠናከር ብሎም በቀጠናው ውስጥ ሰላምና ጸጥታን ለማስፈን ከመቼውም ጊዜ በላይ ተቀራርቦ ለመስራት ያላቸውን ቁርጠኝነት  ማረጋገጣቸውን ከውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡