የሀገር ውስጥ ዜና

የአፍሪካዊያን ችግሮች በአፍሪካዊያን መፍትሄ ማግኘት አለባቸው – የአልጄሪያ ፕሬዚዳንት አብደልማዲድ ተቦኒ

By Meseret Demissu

June 25, 2020

አዲስ አበባ ፣ሰኔ 18 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአፍሪካዊያን ችግሮች በአፍሪካዊያን መፍትሄ ማግኘት አለባቸው ሲሉ የአልጄሪያ ፕሬዚዳንት አብደልማዲድ ተቦኒ ገልጸዋል።

ፕሬዝዳንቱ ይህንን የተናገሩት በአልጄሪያ የኢ᎐ፌ᎐ዲ᎐ሪ ልዩ መልእክተኛ እና ባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩት አምባሳደር አሚን አብዱልቃድር የስራ ጊዜያቸዉን በማጠናቀቃቸው በትናትናው እለት  በነበራቸው የስንብት ውይይት ወቅት ነው።

ፕሬዚዳንት አብደልማዲድ ኢትዮጵያ በናይል ወንዝ ፍትሀዊ ተጠቃሚነትና በሌሎች የታችኛው የተፋሰስ ሀገራትም ጉልህ ጉዳት ላለማድረስ እያደረገች ያለውን ጥንቃቄ በበጎ እንደሚመለከቱትም ገልጸዋል።

የአፍሪካ አገሮች ችግሮች በአፍሪካዊያን በራሳቸው መፈታት ይገባቸዋል የሚል እምነት ያላቸው መሆኑን ጠቁመው÷የኢትዮጵያ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጉዳይም በአፍሪካ ማዕቀፍ እንዲታይ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ከሆኑት ሙሳ ፋኪ ጋር እንዲሁም የወቅቱ የጉባኤው ሊቀ መንበር ከሆኑት የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሰርል ራማፎሳ ጋር መወያየታቸውንም ፕሬዝዳንት አብደልማዲድ ገልፀዋል።

በተጨማሪም በኢትዮጵያና በአልጄሪያ መካከል ያለውን መልካም ግንኙነት የበለጠ ለማሳደግ በሚደረገው እንቅስቃሴ የመንግስታቸው ሁለንተናዊ ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።

በዚህም በቀጣይ የቀጥታ የአየር በረራ ጨምሮ ሌሎች የኢኮኖሚ ትስስሮች ላይ በቅርርብና ትብብር እንደሚሰራ  ፕሬዝዳንት አብደልማዲድ ገልጸዋል።

አምባሳደር አሚን አብደልቀድር በበኩላቸው÷ በኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን መካከል እየተካሄደ ስላለው የሶስትዮሽ ድርድር ገለፃ አድርገውላቸዋል።

ከህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ያለው የአቋም ልዩነትም ሁሉንም እኩል እና ፍትሃዊ ተጠቃሚ በሚያደርግ የመተባበር መርህ ሊካሄድ እንደሚገባው ኢትዮጵያ ጽኑ አቋም እንዳላትም አምባሳደሩ ማስረዳታቸውን ከውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።