የሀገር ውስጥ ዜና

ወንጀለኛ የነበሩ 178 የሠራዊት አባላት ይቅርታ ተደረገላቸው

By ዮሐንስ ደርበው

September 10, 2024

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5፣ 206 (ኤፍ ቢ ሲ) ወንጀለኛ በመሆናቸው እስከ ሞት ፍርድ ተወስኖባቸው ለነበሩ 178 የሠራዊት አባላት በአዲስ ዓመት ይቅርታ መደረጉን የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ከነበረው ግጭት ጋር በተያያዘ አንዳንድ የሠራዊት አባላት የተሰጣቸውን ሕገ-መንግሥታዊ ተልዕኮ ወደ ጎን በመተው በሠራዊቱ እና በሕዝብ ጥቅሞች ላይ ወንጀል መፈፀማቸውን የመከላከያ ሠራዊት ማኅበራዊ ትስስር ገጽ መረጃ አስታውሷል፡፡

ወንጀል መፈፀማቸውን ተከትሎም ጉዳያቸው በወታደራዊ ፍትሕ ሥርዓቱ አማካኝነት ክስ ተመስርቶባቸው በተከሰሱበት ወንጀል ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው በወታደራዊ ፍርድ ቤቶች እስከ ሞት ቅጣት ተወስኖባቸው በማረሚያ ቤት የሚገኙ 178 የሠራዊት አባላት በፈፀሙት ወንጀል ተፀፅተው የይቅርታ ጥያቄአቸውን ለመንግስት እና ለመከላከያ ሚኒስቴር አሥገብተዋል።

የይቅርታ ጥያቄ ማስገባታቸውን ተከትሎ በአንድ በኩል ጉዳያቸው ለይቅርታ ቦርድ ቀርቦ በአዋጅ ቁጥር 840/2006 አንቀፅ 3 ድንጋጌ መሰረት ይቅርታ ማድረግ የሚያሳካቸውን አላማዎች ግምት ውስጥ በማስገባት እና እነዚህ የሰራዊት አባላት በፈፀሙት ወንጀል መፀፀታቸውም ተመልክቷል።

የመከላከያ ሚኒስቴር የይቅርታ ቦርዱን ውሳኔ መሰረት በማድረግ በመታረም ላይ የነበሩ 178 የሠራዊት አባላት ከዛሬ ጳጉሜን 5 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ከእስር በይቅርታ እንዲለቀቁ መወሰኑን አስታውቋል፡፡