የሀገር ውስጥ ዜና

አሜሪካ በመድሎ ከያዘቸው የግድቡ ድርድር ገለል ብላ ለእውነተኛ ድርድር ድጋፍ እንድታደርግ የሀገሪቱ የቀድሞ ባለስልጣናት አሳሰቡ

By Tibebu Kebede

June 26, 2020

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 19፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) አሜሪካ በመድሎ ከያዘቸው የግድቡ ድርድር ገለል ብላ ለእውነተኛ ድርድር ድጋፍ እንድታደርግ የሀገሪቱ የቀድሞ ባለስልጣናት አሳሰቡ።

ባለስልጣናቱ በጉዳዩ ላይ ሀገራቸው ገለልተኛ እንድትሆንና ግልጽና ፍትሃዊ የሽምግልና ሂደትን እንድትከተል ነው የጠየቁት።

አምባሳደር ሱዛን ራይስ፣ አምባሳደር ጀንዳይ ፍሬዘር እና አምባሳደር ሄርማን ኮሆንን ጨምሮ ሰባት የቀድሞ የሃገሪቱ ባለስልጣናት ለአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በጻፉት ደብዳቤ አሁን ላይ ግድቡ ላይ እየተካሄዱ ያሉ ውይይቶች ወሳኝ ምዕራፍ ላይ መድረሳቸውን አንስተዋል።

ከዚህ አንጻርም ዋሽንግተን ከግድቡ ግንባታ ጋር በተያያዘ በገለልተኝነት ልትንቀሳቀስ ይገባታል ብለዋል።

ከዚህ ባለፈም ሃገራቸው ግልጽና ፍትሃዊ የሽምግልና ሂደትን የተከተለ አካሄድ ሊኖራት እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።

የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ ኢትዮጵያ እና ግብፅን እንዲያደራድሩ በደብዳቤያቸው የጠየቁት የአሜሪካ የቀድሞ ከፍተኛ ባለሰልጣናት፥ ዩናይትድ ስቴትስ በግድቡ ላይ እየተካሄደ ካለው ድርድር ገለል እንድትል፣  አደራዳሪዎች በራሳቸው መፍትሄ እንዲፈልጉ እንድታደርግ እና ለጠቅላይ ሚኒስትር ሀምዶክ ድርድር ይፋዊ ድጋፏን እንድትሰጥ ነው ያሳሰቡት።

ሱዳን ከኢትዮጵያ እና ግብፅ ጋር ያላትን ግኑኝነት ሚዛን ጠብቃ ለመሄድ በምታደርገው ጥረት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንዳለች የጠቆሙት ባለስልጣናቱ ፥ ሆኖም ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ መፍትሄ ለመፈለግ ግን የተሻለ ቦታ ላይ እንደምትገኝ ነው ያመለከቱት።

አሁን በግድቡ ላይ አሜሪካ የያዘቸው ገለልተኛ ያልሆነ እና ለግብፅ ያዳላ አቋም በሱዳንም በጦሩ እና በሲቪል አስተዳደሩ መካከል ክፍተት በመፍጠር የሀገሪቱን ሽግግር በማደናቀፍ ሰላምን የሚያናጋ መሆኑን አስጠንቅቀዋል።

ይህን አለመግባባት ለመፍታት አሜሪካ ከአፍሪካ እና ከመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ውጪ የሆነ  ገለልተኛ ሀገር እንዲሳተፍ ልታበረታታ ይገባታልም ብለዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድርድር ወሳኝ ምእራፍ ላይ መግባቱን የጠቆሙት ባለስልጣናቱ፥ የአሜሪካ ብሄራዊ ጥቅም እንዲጠበቅ፣ በአከባቢው ፀጥታና እና መረጋጋት እንዲሰፍን አሜሪካ በዚህ ሂደት ውስጥ ገለልተኛ እንድትሆን እና እውነተኛ ድርድር እንዲካሄድ እንድትደግፍ ነው ያሳሰቡት።