የሀገር ውስጥ ዜና

የአርባ ምንጭ የኮሮና ምርመራ ማዕከል እና አምቦ ዩኒቨርስቲ የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ማእከል ስራ ጀመሩ

By Feven Bishaw

June 26, 2020

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 19፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአርባ ምንጭ የኮሮና ምርመራ ማዕከል እና አምቦ ዩኒቨርስቲ የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ማእከል ስራ ጀመሩ፡፡

ከተከፈተ ቀናትን ያስቆጠረው የአርባ ምንጭ የኮሮና ምርመራ ማዕከል ደረጃውን የጠበቀ ምርመራ ለማድረግ የሚያስችሉ ቁሳቁሶችን በሟሟላት ሂደት ላይ መቆየቱን በደቡብ ክልል የአርባምንጭ ህብረተሰብ ጤና ላብራቶሪ እና የአርባምንጭ ኮሮና ምርመራ ማዕከል ኃላፊ አቶ ከበደ ሞሊሳ ገልፀዋል፡፡

አሁን ላይ ቀጣይነት ባለው መልኩ ምርመራ ማድረግ የሚያስችሉ ቅድመ ሁኔታዎችን በሟሟላት ስራ መጀመሩንም አስታውቀዋል፡፡

በዚህም ከጋሞ እና አጎራባች ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች የተሰበሰቡ 44 ናሙናዎችን መመርመሩን ተገልጿል፡፡

የምርመራ ውጤቶች በክልል ማዕከል ብቻ እንደሚገለፁ የተናገሩት ኃላፊው÷ በማዕከሉ የሚደረጉ የምርመራ ውጤቶችም በክልሉ የጤና ቢሮ በኩል በሀገር አቀፍ ደረጃ ከሚገለጹ ሪፖርቶች ጋር በአንድ ላይ የሚቀርቡ ይሆናል ብለዋል፡፡

በቀን እስከ 400 የሚደርሱ ናሙናዎችን የመመርመር አቅም ያለው ማዕከሉ ለጋሞ፣ ጎፋ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ኮንሶ ፣ እና ከደራሼ ዞኖች፣ ቡርጂ፣ አማሮ እና አሌ ልዩ ወረዳዎች ለሚመጡ ናሙናዎች የ24 ሰዓታት የምርመራ አገልግሎት እንደሚሰጥ የጋሞ ዞን የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

በተመሳሳይ በአምቦ ዩኒቨርስቲ የተቋቋመው የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ማእከል ተመርቆ ስራ ጀምሯል።

ላብራቶሪውን የመረቁት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ድጉማ ፣ የአምቦ ከተማ ከንቲባ እና የኦሮሞያ ክልል ጤና ቢሮ ሃላፊ ዶክተር መንግስቱ በቀለ ናቸው።

ይህ ላብራቶሪም በቀን እስከ 1ሺህ ናሙናዎችን መመርመር እንደሚችል የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ገልፀዋል።

ማዕከሉን ለመገንባትም 10 ሚሊየን ብር ገደማ ወጪ እንደተደረገ ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል።

 

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።