አዲስ አበባ፣ ሰኔ 20፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጉዳይን ወደ አፍሪካ ህብረት ማምጣት መቻሉ ለኢትዮጵያ ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ ድል መሆኑ ተገለፀ።
የሶስት የአፍሪካ ሀገራት ጉዳይ የሆነውን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጉዳይን ግብፅ ወደ አረብ ሊግ እና ወደ ተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት በመውሰድ አፍሪካዊ ይዘቱን ለማሳጣት ሰትሰራ እንደነበር ይታወሳል።
የአፍሪካ ሀገራት የህዳሴ ግድብ ጉዳይን እንዲመለከት መደረጉ ሌሎችም አካላት ጉዳዩ በህብረቱ እንዲታይና መፍትሄ እንዲያገኝ አቋም እንዲይዙ የሚያስችል መሆኑን ይህም ለኢትዮጵያ ስኬት መሆኑን ነው አስተያየት ሰጪዎች የተናገሩት።
የአረብ ሊግ እና የፀጥታው ምክር ቤት ጉዳዩ በአፍሪካ ህብረት እንዲታይ አቋም እንዲይዙ ተፅእኖ መፍጠር የሚችልም ነው ብለዋል።
ግድቡን ውሃ ሙሌት ለማስጀመር የሚያስችሉ ቀሪ ስራዎች እስከሚጠናቀቁ ድረስ በጉዳዩ ላይ ስምምነት እንዲደረስ ማድረጓም ሌላው ድሏ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካዊ እና ቀጠናዊ መርህ በጋራ ተጠቃሚነት ለሁሉም ዜጎች ተጠቃሚነት እና ማንንም በማይጎዳ ይልቁንም አብሮ በማደግ ትስስርን የሚያጠናክረው ፕሮጀክቱ በሌሎች ዘንድ እምነት አንዲጣልበትና ግንዛቤ እንዲያዝ እየተደረገ ያለው ጥረት ውጤታማ መሆኑን ያሳያለም ነው ያሉት።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የትናንቱን ስብሰባ በተመለከተ የግድቡን የውሃ ሙሌት አጀንዳ በውይይቱ እንዳልተነሳና ኢትዮጵያን ኢትዮጵያም ይህንን በተመለከተ የገባችው ቃልም ሆነ ግዴታ እንደሌለ ጉዳዩን የተከታተሉ የዲፕሎማቲክ ምንጮች ገልፀውልናል።
በግብፃውያን በኩል የተያዘው የማያቀራርብና ራስን ብቻ ማዕከል ያደረገ ግትር አቋም በትናንቱም ስብሰባ ላይ እንደተንፀባረቀ የገለፁት እነዚህ ምንጮች ከስብሰባው በኋላ ያሰራጩት የፕሮፖጋንዳ ስራ ዜጎችን ተራ የማሳሳት ተግባር ነው ብለዋል።
ግብፃውያኑ የራሳቸውን ህዝብ እና ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ያከበረ የመረጃ ስርጭት ቢከተሉ የተሻለ አማራጭ መሆኑን ሊገነዘቡ ይገባልም ነው ያሉት።