የሀገር ውስጥ ዜና

ምክር ቤቱ 476 ነጥብ 12 ቢሊየን ብር ሆኖ የቀረበለትን የፌዴራል መንግስት የ2013 በጀት አፀደቀ

By Tibebu Kebede

July 07, 2020

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 30፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዛሬው እለት መደበኛ ስብሰባውን አካሂዷል።

ምክር ቤቱ በዛሬው መደበኛ ስብሰባው በ2013 በጀት ዓመት በፌዴራል መንግሥት ረቂቅ በጀት ላይ ተወያይቷል።

የ2013 በጀት ዓመት በፌዴራል መንግሥት ረቂቅ በጀት 476 ቢሊየን 12 ሚሊየን 952 ሺህ 445 ብር እንዲሆን መወሰኑ ይታወቃል።

በምክር ቤቱ ስለ በጀቱ ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ፥ በጀቱ ድህነት ቅነሳ እና አጠቃላይ ምርታማነትን ለማሳደግ የሚሰሩ ስራዎችን ለማስቀጠል በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

ባለፉት የለውጥ ዓመታትም የበጀት ጉድለትና የእዳ ጫናን በመቀነስ የሀገር ውስጥ የምርት እድገትን ማሳደግ መቻሉንም ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ አክለውም፥ ኢትዮጵያ ለውጡ ከመጣ ወዲህ አጠቃላይ ሀገራዊ ሃብቷ ወይም ጂ ዲ ፒዋ በእጅጉ ማደጉን ተናግረዋል።

በዚህም ከለውጡ በፊት 2 ነጥብ 2 ትሪሊየን ብር የነበረው የሀገሪቱ ጂዲፒ አሁን ላይ ወደ 3 ነጥብ 4 ትሪሊየን ብር አድጓል ብለዋል።

ከዛም ባለፈ የሀገሪቱ የበጀት መጠን በከፍተኛ ሁኔታ ያደገ መሆኑን በማንሳት፥ በተለይም ድህነት ቅነሳ ላይ ላተኮሩ ዘርፎች የተመደበ በጀት ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየቱንም ገልፀዋል።

በዚህም በ2013 በጀት ዓመት ለሚከናወኑ ሥራዎችና አገልግሎቶች የሚያስፈልገውን ለፌዴራል መንግሥት መደበኛ ወጪዎች ብር 133 ቢሊየን 321 ሚሊየን 561 ሺህ፣ ለካፒታል ወጪዎች ብር 160 ቢሊየን 329 ሚሊየን 788 ሺህ፣ ለክልሎች የሚሰጥ ድጋፍ ብር 176 ቢሊየን 361 ሚሊየን 602 ሺህ፣ ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ድጋፍ ብር 6 ቢሊየን፤ በጠቅላላው 476 ቢሊየን 12 ሚሊየን 952 ሺህ 445 ብር ነው የተያዘው።

የ2013 በጀት ግብዓትን ከውጤት ጋር የሚያዛምድ እንዲሁም ኮሮና ቫይረስ የሚያስከትለውን ተጽዕኖ ለመቋቋም ታሳቢ ተደርጎ መዘጋጀቱ ተገልጿል።

በ2013 በጀት ዓመት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በ8 ነጥብ 5 በመቶ እድገት እንደሚያስመዘግብ የተጠቀሰ ሲሆን፥ የማክሮ ኢኮኖሚው ከገጠመው ተግዳሮት እንዲላቀቅ መንግስት ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ቀርጾ በመተግበር ላይ መሆኑንም አስታውቀዋል።

ምክር ቤቱም በዛሬው እለት ባካሄደው መደበኛ ስብሰባው በ2013 በጀት ላይ ከተወያየ በኋላ በሙሉ ደምጽ አጽቆታል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።