የሀገር ውስጥ ዜና

ምክር ቤቱ የ5 ሚኒስትሮችን ሹመት አጸደቀ

By Shambel Mihret

October 29, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 19፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ስብሰባ የአምስት ሚኒስትሮችን ሹመት በአንድ ተቃውሞና በሁለት ድምፀ-ተዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ አጸደቀ፡፡

ሹመታቸው የጸደቀላቸው ከፍተኛ አመራሮችም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጤሞቲዎስ (ዶ/ር)፣ የፍትሕ ሚኒስትር ሃና አርዓያ ሥላሴ፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)፣ የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ እና የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ናቸው፡፡

በተጨማሪም የምክር ቤቱ 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 1ኛ መደበኛ ስብሰባ ቃለ ጉባዔ ጸድቋል፡፡

እንዲሁም ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ መስከረም 27 ቀን 2017 ዓ.ም ለሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ መደበኛ ስብሰባ ያደረጉትን የመክፈቻ ንግግር አስመልክቶ የቀረበውን የድጋፍ ሞሽን ካዳመጠ በኋላ አፅድቋል።

በስብሰባው የከተማ መሬትን በሊዝ ለመያዝ የቀረበ ረቂቅ አዋጅ፣ የከተማ መሬት ይዞታ እና መሬት ነክ ንብረት ለመመዝገብ የቀረበ ረቂቅ አዋጅ ለከተማና መሰረተ ልማት ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል፡፡

በተጨማሪም ምክር ቤቱ የአጠቃላይ ትምህርት ረቂቅ አዋጅን መርምሮ በአንድ ተቃውሞ በአብላጫ ድምጽ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መርቷል፡፡

እንዲሁም ምክር ቤቱ የመገናኛ ብዙኃን ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ ለዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል፡፡

በየሻምበል ምኅረት እና ዓለምሰገድ አሳዬ