የሀገር ውስጥ ዜና

“የፓርቲያችን አባላት በሥነ-ምግባር ታንፀው እንዲያገለግሉ እየተሠራ ነው”- አቶ አደም ፋራህ

By ዮሐንስ ደርበው

October 29, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 19፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የብልጽግና ፓርቲ አባላት በሥነ-ምግባር ታንፀው ሕዝቡን እንዲያገለግሉ ሰፊ ሥራ እየተሠራ መሆኑን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪ ማዕከል ኃላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ገለጹ፡፡

የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን አባላት ከቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ የኢንስፔክሽና ሥነ-ምግባር ኮሚሽን አመራሮች ጋር በቤጂንግ ተወያይተዋል፡፡

አቶ አደም በዚሁ ወቅት ጠንካራ ፓርቲ ለመመስረት ጠንካራ የሥነ-ምግባር እና ኢንስፔክሽን ኮሚሽን የላቀ ሚና እንዳለው ገልጸዋል፡፡

ከዚህ አንጻር ብልጽግና ፓርቲ የውስጥ ቁጥጥሩን ለማጠናከር በርካታ ሥራዎችን መጀመሩንና ከዚህ አንጻር የረጅም ጊዜ ልምድ ካለው ሲፒሲ ተጨማሪ ተሞክሮዎችን ለመቅሰም ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

ብልጽግና ፓርቲ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ አባላትን በማፍራት መዋቅሩን እያስፋፋ መሆኑን ገልጸው÷ አባላቱ በሥነ-ምግባር ታንፀው ሕዝብን እንዲያገለግሉ ሰፊ ሥራ እየሠራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ለዚህም በጉባዔ የተመረጠና ከላይ እስከ ታች የተዋቀረ ጠንካራ የሥነ-ምግባር እና የኢንስፔክሽን ኮሚሽን እየተገነባ ነው ማለታቸውን የብልጽግና ፓርቲ መረጃ አላክቷል፡፡

የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ የሥነ ምግባር ኢንስፔክሽን ኮሚሽን አመራር ዋንግ ሺንቺ በበኩላቸው÷ በፓርቲያቸው የውስጥ ኢንስፔክሽን አስፈላጊ የሆነበትን ምክንያት፣ የኮሚሽኑን ተግባራትና ኃላፊነቶች፣ ያከናወናቸውን ሥራዎች እና የአሠራር ሥርዓቱን በተመለከተ አብራርተዋል፡፡

አንድ ፓርቲ ለሕዝብ ለገባው ቃል ታማኝ ሆኖ እንዲቀጥል እና በተለይም የአባላቱ ብዛትም ሆነ የፓርቲው መዋቅር እየሰፋ ሲሄድ ውጤታማነትን ከግልፅነትና ተጠያቂነት ጋር አስጠብቆ ለመቀጠል የውስጥ ሥነ-ምግባርና ቁጥጥር ወሳኝ ነው ሲሉም አስገነዝበዋል፡፡