የሀገር ውስጥ ዜና

ኮይካ ኢትዮጵያ በዲጂታል ልማት እያደረገች ያለችውን ጥረት እንደሚደግፍ ገለፀ

By Feven Bishaw

October 29, 2024

 

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 19፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኮሪያ ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ (ኮይካ) ኢትዮጵያ በዲጂታል ልማት እያከናወነች ያለውን ጥረት እንደሚደግፍ አስታወቀ።

በኢትዮጵያ የኮይካ ዳይሬክተር ሀን ዲዮግ ቾ ÷ በኢትዮጵያ የአምራችና የጤናውን ዘርፍ እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋምና አካታች ልማትን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት እንደሚደግፉ ገልፀዋል።

ኮይካ በዲጂታል ዘርፉም ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው÷ የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት አሰጣጥን እየደገፈ መሆኑን አንስተዋል።

በአይሲቲ ዘርፍ ያሉ ስታርትአፖችን በአቅም ግንባታና በገንዘብ እየደገፉ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ባለንበት ዘመን ኢኮኖሚን ለማሳደግና ማህበረሰብን ለማበልፀግ ዲጂታል እውቀት የግድ መሆኑን ጠቅሰው ÷ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያ መንግስት ዲጂታላይዜሽን ላይ እያከናወነ ያለው ተግባር የሚበረታታ እንደሆነ ገልጸዋል።

በእያንዳንዱ የልማት ትብብሮች የተለያዩ መርሃ ግብሮች እየተከናወኑ መሆናቸውንና ለዚህም 150 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በጀት እንደተመደበ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡