አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 19፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢኮኖሚ እድገትን ለማራመድና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ፖሊሲ ማስፈጸሚያ ስትራቴጂ ወደ ስራ መግባት ወሳኝ ነው ሲሉ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን (ኤስ ቲ አይ) ፖሊሲ ማስፈጸሚያ ስትራቴጂ ስነድ ላይ ያዘጋጀው አውደ ጥናት እየተካሄደ ነው፡፡
በወርክሾፑ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን (ኤስ ቲ አይ) ፖሊሲ ማስፈጸሚያ ስትራቴጂ ለሚኒስትሮች፣ ለፌደራል ተቋማት ከፍተኛ ሃላፊዎች እንዲሁም ለክልል ቢሮ ሃላፊዎች እና ጥሪ ለተደረገላቸው አካላት ቀርቧል።
በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ÷ የፖሊሲ ማስፈጸሚያ ስትራቴጂው ኢትዮጵያን መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለማሸጋገር ያለመ ሀገራዊ ስትራቴጂ ነው ብለዋል።
የሳይንስና ቴክኖሎጂን ሃይል በመጠቀም የኢኮኖሚ እድገትን ለማራመድ፣የኑሮ ደረጃን ለማሻሻል እና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ የተያዘውን ርዕይ እውን ለማድረግ የስትራቴጂው ወደ ስራ መግባት ወሳኝ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
ስትራቴጂው ሁሉንም ሴክተሮች የሚዳስስ መሆኑን ጠቁመው÷ በዚህ ዘርፍ ውጤታማ ለመሆን ዝግጁ እንዲሆኑ ማስገንዘባቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡