የሀገር ውስጥ ዜና

ትንኮሳዎችን ለመቅጨት የውስጥ ችግርን መፍታት ይገባል- አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን

By Shambel Mihret

October 29, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 19፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የሚያጋጥሙንን ትንኮሳዎች በአጭር ለመቅጨት የውስጥ ችግራችንን መፍታትና ተባብሮ መሥራት ያስፈልጋል ሲሉ የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ገለጹ፡፡

አምባሳደር ሬድዋን በመከላከያ ዋር ኮሌጅ ተገኝተው በሀገራዊ እና ቀጣናዊ የደኅንነት ጉዳዮችና ስጋት ትንተና ዙሪያ ለ3ኛ ዙር መደበኛ ተማሪዎች ገለፃ አድርገዋል።

በዚሁ ወቅትም የአንድን ሀገር ብሔራዊና ታሪካዊ ስጋት መለየትና መተንተን÷ ግልፅ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ለመቅረፅ ብሎም በቂ ምላሽ መስጠት የሚችሉ የማስፈፀሚያ መሳሪዎችን ለመገንባት ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

የኢትዮጵያን ብሔራዊ ደኅንነት ለመጠበቅ÷ በእውቀትና በኢኮኖሚ መጎልበት ብሎም የሕዝብ ሁለንተናዊ ደኅንነትና አንድነት በፅኑ መሰረት ላይ የተገነባ መሆን እንዳለበትም አስረድተዋል፡፡

ይህንን ለማድረግ ደግሞ ከድህነትና ከተረጅነት መላቀቅ እንደሚገባ በመግለጽ አቅምን ማጎልበትና ወደ ተሻለ ደረጃ ማሻገር ያስፈልጋል ማለታቸውን የመከላከያ ሠራዊት ማኅበራዊ ትስስር ገጽ መረጃ አመላክቷል፡፡

በውስጥና በውጭ የሚያጋጥሙን ትንኮሳዎች በአጭሩ ለመቅጨትም የውስጥ ችግርን መፍታትና ተባብሮ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ሀገራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ በጎራና በመንደር ሳንከለል በአንድነት ሆነን የኢትዮጵያን ልዕልና ማስጠበቅ አለብን ሲሉም ገልጸዋል፡፡

የአንድን ሀገር ዳር ድንበር እና ብሔራዊ ደኅንነት ለማስጠበቅ የሁሉም ማኅበረሰብ ርብርብና ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡

የመከላከያ ዋር ኮሌጅ አዛዥ ብርጋዲየር ጄኔራል ቡልቲ ታደሰ በበኩላቸው÷ ብሔራዊ ደኅንነትን ለማስጠበቅ የዜጎች ንቁ ተሳትፎ አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ለዚህም እንደ ሀገር በአንድነት መቆምና በሀገር ፍቅር ስሜት መነሳሳት ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡