አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 8፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአክሱም ሃውልት ጥገና በመጭው ነሃሴ ወር ለመጀመር አስፈላጊው መሳሪያ ከጣሊያን ወደ አክሱም መግባቱን የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን አስታወቀ።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሙሉጌታ ፍስሃ እንደገለፁት የአክሱም ሐውልትን ከተደቀነበት የመውደቅ አደጋ ለመታደግ በመጭው ነሐሴ ጥገና ይጀመራል።
ለጥገናው የሚያስፈልጉ አስፈላጊ መሳሪያዎች ከጣሊያን ወደ አክሱም ከተማ ሰሞኑን መግባታቸውን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
የሐውልቱን ጥገና ባለፈው መጋቢት ወር ለመጀመር ታቅዶ የነበረ ቢሆንም የኮሮና ቫይረስ መከሰትን ተከትሎ እስካሁን ድረስ መቆየቱን አስረድተዋል።
መንግስት ለጥገናው ተገቢ ትኩረት ሰጥቶ ከጣሊያን መንግስት ጋር በመነጋገር ስምምነት ላይ በመድረሱ ለስራው የሚያስፈልጉ መሳሪያዎች በሙሉ ወደ ቦታው እንዲደርሱ ማድረግ ተችሏልም ነው ያሉት።
የጥገና ስራውን በስድስት ወራት ውስጥ ለማጠናቀቅ መታቀዱን ዋና ዳይሬክተሩ ማስታወቃቸውንም ኢዜአ ዘግቧል።
የአክሱም ከተማ ነዋሪ አቶ ሃፍቶም አሰፋ በሰጡት አስተያየት የሃውልቱ ጥገና በመዘግየቱ ምክንያት በአካባቢው ነዋሪዎች ዘንድ ስጋት አሳድሮ ቆይቷል።
አሁን ግን መሳሪያዎቹ ወደ ቦታው በመድረሳቸውና ጥገናው ይጀምራል በመባሉ እፎይታ ተሰምቶናል ብለዋል።