የሀገር ውስጥ ዜና

ወ/ሮ ዓለሚቱ ኡሞድ የሕዝቡን ሕይወት ለመለወጥ እየተሠራ መሆኑን ገለጹ

By ዮሐንስ ደርበው

November 10, 2024

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 1፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላ ክልል ያለውን እምቅ የተፈጥሮ ሀብት በአግባቡ በማልማት የሕዝቡን ሕይወት ለመለወጥ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መሥተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ አስታወቁ።

ርዕሰ መሥተዳድሯ በጋምቤላ ወረዳ በቦንጋና በኮበን ቀበሌ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎችን በጎበኙት ወቅት እንዳሉት÷ የጋምቤላ ክልል እምቅ የውኃ፣ የመሬት፣ የማዕድን፣ ምቹ የአየር ፀባይ እና የሰው ኃይል የታደለ ነው፡፡

በክልሉ ያለውን ፀጋ ወደ ልማት በመለወጥ የሕዝቡን ኑሮ ለማሻሻል የተጀመሩ ሥራዎች ጥሩ ቢሆኑም በቂ እንዳልሆኑ መናገራቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ አመላክቷል፡፡

በመሆኑም የተገኘውን አንፃራዊ ሰላም በመጠቀም ያለውን ሀብት በማልማት የሕዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል፡፡

በክልሉ ያለውን ጸጋ በአግባቡ ማልማት ከተቻለ ለአካባቢው ማኅበረሰብ ብቻ ሳይሆን ለሌላው የኢትዮጵያ አካባቢ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ጭምር ትልቅ ፋይዳ እንዳለው በመገንዘብ አመራሩ በቁርጠኝነት እንዲሠራ አሳስበዋል።

በተለይም የወርቅ አምራቾች ሕጋዊ መስመር እንዲይዙ በመቆጣጠር ሀብቱን ለሀገር የኢኮኖሚ ግንባታ ለማዋል በትኩረት ይሠራል ሲሉ በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡