አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 10፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በደምቢዶሎ ተማሪዎችን አግተዋል በሚል የተጠረጠሩ 17 ግለሰቦች በሽብር ወንጀል ክስ ተመሰረተባቸው።
በዛሬው ዕለት በእነ ከሊፋ አብዱረሂማን በሚጠራው የክስ መዝገብ ውስጥ 17 ግለሰቦች በጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በየደረጃው 3 ክሰ ተመስርቶባቸዋል።
ክሱ በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 1ኛ ተረኛ የወንጀል ችሎት እነ ከሊፋ አብዱረሂማን የክስ መዝገብ 17ቱ ተከሳሾች ላይ የተመሰረተ ሲሆን ከ17ቱ ተከሳሾች መካከል በቁጥጥር ስር የዋሉት 10 ተከሳሾች ናቸው።
ፍርድ ቤቱ ዛሬ ማንነታቸውን ያረጋገጠ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ተከሳሽ በጊዜ ቀጠሮ ላይ እንዳለ በዋስ ተፈቷል።
ሁለቱ በኮቪድ19 ወረርሽን በመጠርጠራቸው በለይቶ ማቆያ እንዲገቡ ሲደረግ ቀሪ ሰባት ተከሳሾች ግን ፍርድ ቤት ቀርበዋል።
የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ሶስት ክስ የመሰረተባቸው ሲሆን ተከሳሾቹ ወንጀሉን የፈጸሙት በህዳር 24 እና 25 ቀን 2012 ዓ.ም ነው።
በዚህ በተጠቀሰው ጊዜ ወደ ቤተሰብ እየተመለሱ የነበሩ የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን በማገት እና መረጃውን ለጸጥታ አካል በመሸሸግ ወንጀል በአጠቃላይ በየደረጃው ሶሰት ክስ ነው የቀረበባቸው።
ከ1ኛ እስከ 14ኛ ያሉት ተከሳሾች በቀጥታ መሳተፍ ወንጀል የተከሰሱ ሲሆን 15ኛ ተከሳሽ የኦነግ ሸኔ አባልና አስተባበሪ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ተከሳሹ ከላይ በተጠቀሰ ጊዜ የታገቱ አምስት ወንድና አንድ ሴት ተማሪዎችን በመኖሪያ ቤቱ በመደበቅ ወደ ጫካ ለመውሰድ ባለማሳወቅ ክስ አቅርቦበታል።
በሁለተኛ ክስ ደግሞ ረዳትና ሹፌር የሆኑት ተከሳሾች ከመንገድ ዘግተው ተማሪዎችን በማገት ጫካ ወስደው ለኦነግ ሸኔ አሳልፈው መስጠታቸውን ዐቃቤ ህግ በክሱ ጠቅሷል።
ሁለቱ ክሶች በፀረ ሽብር አዋጅ 652/2001 አንቀጽ 3 ንዑስ ቁጥር ሶስት መሰረት የተፈፀመን የእገታና ጠለፋ የሽብር ወንጀልን የተመለከቱ ናቸው፡፡
ሶስተኛው ክስ ደግሞ አንደኛው ተከሳሽ ተማሪዎቹ በጫካ ውስጥ እየተጓዙ ሳለ መሽቶባቸው ታጋቾች መሆናቸውን እያወቀ መኖሪያ ቤቱ በማሳደሩ እና ለየትኛውም የመንግስት አካል ባላማሳወቁ የሽብር ወንጀልን ባለማሳወቅ ወንጀል በሚል የቀረበ ክስ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
በዚህ መልኩ የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ክስ ያቀረበባቸው እና በችሎት የተገኙት ሰባቱ ተከሳሾች ክሱን ጠበቃ አቁመን ይነበብልን ማለታቸውን ተከትሎ ፍርድ ቤቱ በጠበቃ ክሱ እንዲነበብላቸው አዟል።
ክሱን በጠበቃ በችሎት ለማስደመጥም ፍርድቤቱ ለሃምሌ 30 ቀን 2012 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
በታሪክ አዱኛ