ዓለምአቀፋዊ ዜና

ዓለም ላይ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ14 ሚሊየን አልፏል

By Tibebu Kebede

July 18, 2020

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 11፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ዓለም ላይ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ14 ሚሊየን ማለፉ ተገለጸ።

እንደ ጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ መረጃ ዓለም ላይ በየቀኑ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ዳግም እያሻቀበ ነው።

በትናንትናው እለትም 237 ሺህ 743 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል።

ከዚህ ውስጥ በአሜሪካ 77 ሺህ 638 ሰዎች በኮሮና ቫይረስ በአንድ ቀን መያዛቸው ታውቋል።

አሁን ላይም በአሜሪካ 3 ሚሊየን 640 ሺህ ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ139 ሺህ 128 ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ሳቢያ ለህልፈት ተዳርገዋል።

በብራዚል ከ2 ሚሊየን በላይ እንዲሁም በህንድ ከ1 ሚሊየን በላይ ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል።

ከዚህ ባለፈም በሜክሲኮ እና ጀርመን በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መጨመሩንም የጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ መረጃ ያመላክታል።

ዓለም ላይ በቫይረሱ ሳቢያ ከ600 ሺህ በላይ ሰዎች ለህልፈት ሲዳረጉ ከ7 ነጥብ 8 ሚሊየን በላይ ሰዎች ደግሞ አገግመዋል።

ምንጭ፣ አልጀዚራ እና ቢቢሲ