የሀገር ውስጥ ዜና

የተማሪዎችን ውጤትለማሻሻል የትምህርት ማህበረሰቡ የበኩሉን ሊወጣ ይገባል – አቶ አሻድሊ ሃሰን

By Melaku Gedif

November 21, 2024

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 12፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተማሪዎችን ውጤትና ሥነምግባር ለማሻሻል በሚደረገው ጥረት የትምህርት ማህበረሰቡ የበኩሉን ሚና ሊወጣ ይገባል ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሃሰን ገለጹ።

አቶ አሻድሊ የተማሪዎችን ውጤትና ሥነ-ምግባር ማሻሻል በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ በየደረጃው ከሚገኙ የትምህርት አመራሮችና ርዕሳነ-መምህራን ጋር መክረዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በዚህ ወቅት÷ ባለፉት ዓመታት በትምህርቱ ዘርፍ ያጋጠሙትን ስብራቶች ለመጠገን በርካታ ተግባራት ተሰርቷል ብለዋል።

በክልሉ በነበረው የፀጥታ ችግር ጫና ውስጥ ከነበሩት ተቋማት የትምህርቱ ዘርፍ አንዱ መሆኑን ጠቁመው÷ ለዘርፉ በሰጠው ትኩረት የወደሙ የትምህርት ተቋማትን በመልሶ በማቋቋም የተዘጉ ት/ቤቶች እንዲከፈቱ መደረጉን ጠቅሰዋል።

በክልሉ አብዛኛው የትምህርት ተቋማት ከደረጃ በታች መሆናቸው ለትምህርት ጥራቱ ችግር መሆኑን ያነሱት አቶ አሻድሊ÷ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል በትኩረት መሥራት ይገባል ብለዋል።

ወቅቱ የሚጠይቀውን ብቁ እና ተወዳዳሪ ዜጋን ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት የትምህርት አመራሩ እና ማህበረሰብ የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባም አቶ አሻድሊ አሳስበዋል።