የሀገር ውስጥ ዜና

አብርሃም በላይ(ዶ/ር) የመገጭ ግድብን የስራ እንቅስቃሴ ጎበኙ

By yeshambel Mihert

November 30, 2024

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 21፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የመስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር አብርሃም በላይ(ዶ/ር) የመገጭ ግድብን የስራ እንቅስቃሴ ጎበኙ ።

በጉብኝቱ ከሚኒስትሩ በተጨማሪ የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮችና የጎንደር ከተማ የስራ ሀላፊዎች ተሳትፈዋል።

 

አብርሃም በላይ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት ÷ የመገጭ ግድብ በተለያዩ ምክንያቶች ለ15 ዓመታት ዘግይቶ እንደቆየና ማህበረሰቡ ከፍተኛ ቅሬታ ሲያነሳበት እንደነበር አስታውሰዋል።

በቀደመው ጊዜ በመገጭ ፕሮጀክት የታዩ ችግሮች ተፈተው ስራው በጥሩ መንገድ እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የፕሮጀክቱ የቆዩ ችግሮች በውጭና ሀገር ውስጥ አማካሪዎች ተለይቶ ወደ ስራ መገባቱ አሁናዊ የፕሮጀክቱ አፈፃፀም ለውጥ እንዲያመጣ አድርጓልም ብለዋል፡፡

መንግስት ለፕሮጀክቱ በሰጠው ትኩረት በቀደመው ጊዜ በፕሮጀክቱ የነበሩ የጥራትና የፕሮጀክት አስተዳደር ችግሮችን መፍታት በሚያስችል መንገድ ስራዎቹ እንዲመሩ ተደርገዋልም ብለዋል ሚኒስትሩ።

አሁናዊ የፕሮጀክቱ ስራ መሻሻል የታየበት ነው ያሉት አብርሃም(ዶ/ር) በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ መንግስት ቁርጠኛ ሆኖ እየሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡

በምናለ አየነው