የሀገር ውስጥ ዜና

ብርጋዲየር ጄኔራል ሰይፈ ኢንጊ ጉራሮ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ

By amele Demisew

November 30, 2024

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 21፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) እናት ሀገራቸውን ለ35 ዓመታት በውትድርና ሙያ ያገለገሉት ብርጋዲየር ጄኔራል ሰይፈ ኢንጊ ጉራሮ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡

ብርጋዲየር ጄኔራል ሰይፈ ኢንጊ ከአባታቸው ከአቶ ኢንጊ ጉራሮ እና ከእናታቸው ወ/ሮ ተሸቴ ፋኔ በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ሙኔሳ ወረዳ ጃዊ አሳርጌ ከተማ 01 ቀበሌ ግንቦት 1ቀን 1962 ዓ.ም ነበር የተወለዱት፡፡

በህዝቦች ላይ እየደረሰ የነበረውን ጭቆና በመቃወም በ1982 ዓ.ም ወደ ውትድርናው ዓለም የተቀላቀሉት ብርጋዲየር ጄኔራል ሰይፈ ኢንጊ በተለያዩ የውትድርና አመራር እርከኖች ሀገራቸውን በታማኝነት፣ በቅንነትና በጀግንነት አገልግለዋል፡፡

ብርጋዲየር ጄኔራል ሰይፈ ኢንጊ በ1990 ዓ.ም ኤርትራ ኢትዮጵያ ሀገራችንን በወረረችበት ወቅት በተከዜ ልዩ ብርጌድ በሻምበል አዛዥነት በጀግንነት ከተወጡ በኋላ ወደ 44ኛ ዳሎል ክፍለ ጦር በመዛወር የሬጅመንት ምክትል አዛዥ ሆነው እስከ 1999 ዓ.ም ኃላፊነታቸውን በተገቢው ተወጥተዋል፡፡

ብርጋዴር ጄኔራል ሰይፈ ኢንጊ በ1999 ዓ.ም አልሸባብ በሀገራችን ኢትዮጵያ ላይ ጀሀድ ባወጀበት ወቅት ከኢዳሌ እስከ ሞቃዲሾ በተካሄደው እልህ አስጨራሽ ውጊያና ጠላትን በመደምሰሱ ሂደት በሳል አመራር ከሰጡና አንፀባራቂ ድል ካስመዘገቡ የቁርጥ ቀን የኢትዮጵያ ጀግኖች መካከልም አንዱ ነበሩ፡፡

ከ2001 ዓ.ም እስከ 2010 በ44ኛና በ12ኛ ክፍለጦር በሬጅመንት ምክትልና በሬጅመንት አዛዥነት ተመድበው የሰሩት ብርጋዲየር ጀኔራል ሰይፈ ኢንጊ እስከ 2013 ዓ.ም የምዕራብ ዕዝ ማሰልጠኛ ማዕከል አዛዥ ሆነው አገልግለዋል፡፡

ከሚያዚያ 2013 ዓ.ም እስከ ጥር 2015 ዓ.ም በነበሩት ጊዜያትም የ22ኛ ንስር ክፍለ ጦር አዛዥ በመሆን ተመድበው ስራቸውን በፍፁም ታማኝነት፣ ቅንነትና ጀግንነት መዋጣት የቻሉ ጀግና መሪ ነበሩ፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ለማደናቀፍ ዕለት ከዕለት የሚጠነሰሱ ሴራዎችን በማምከንና ጸረ-ሰላም ኃይሎችን በመደምሰስ ግንባታው ለፍፃሜው ዋዜማ እንዲደርስ እስከ ህልፈተ- ሕይወታቸው ድረስ የተጉና ታሪክ የማይዘነጋው ደማቅ አሻራ ማሳረፍ የቻሉ ጀግና መሪና የሀገር ባለ ውለታ ነበሩ፡፡

ብርጋዴየር ጄኔራል ሰይፈ ኢንጊ ከጥር 2015 ዓ.ም ሕይወታቸው እስካለፈበት ዕለት በምዕራብ ዕዝ ስር የኮር አዛዥ በመሆን ሀገራቸውንና ህዝባቸውን በትጋት አገልግለዋል፡፡

ለ35 ዓመታት ሀገራቸውንና ህዝባቸውን በታማኝነትና በቅንነት ያገለገሉት ብርጋዲየር ጄኔራል ሰይፈ ኢንጊ ቤተሰብ አስተዳዳሪና የአንዲት ሴት ልጅ አባትም ነበሩ።

ጄኔራል መኮንኑ ባደረባቸው ሕመም በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ሕዳር 19 ቀን 2017 ዓ.ም በተወለዱ በ55 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡

ስርዓተ ቀብራቸውም የሰራዊቱ ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዦችና አመራሮችን ጨምሮ ወዳጅ ዘመዶቻቸው በተገኙበት በኮልፌ የሙስሊሞች መካነ መቃብር ዛሬ ሕዳር 21