አዲስ አበባ፣ ሕዳር 21፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ዐይን ባንክ የዓይን ብሌን ልገሣን ለማበረታታት በክልሎቸ ተጨማሪ ማዕከላትን ሊከፍት መሆኑን አስታውቋል።
ባንኩ በኢትዮጵያ የዓይን ብሌን ልገሣን ባህል ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር መክሯል፡፡
የኢትዮጵያ ደምና ህብረ ሕዋሥ ባንክ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አሸናፊ ታዘበው (ዶ/ር) በዚህ ወቅት÷የዓይን ባንክ ማዕከል በአዲሥ አበባ ብቻ መሆኑ በዓይን ብሌን ልገሣ ላይ ክፍተት መፍጠሩን ተናግረዋል።
በዚህም አገልግሎቱን ለማስፋት በተያዘው ወር ተጨማሪ ቅርንጫፍ በጅማ ከተማ ለመክፈት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
ይህም ወደ ማህበረሠቡ ቀርቦ የግንዛቤ ማሥጨበጥ ሥራ ከመሥራት ጀምሮ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች እንደሚኖሩት ነው የገለፁት።
ከሕልፈት በኋላ ከበጎ ፈቃደኞች በሚገኝ የዓይን ብሌን አማካይነት የበርካታ ሰዎችን የዓይን ብርሃን መመለሥ መቻሉን አመልክተዋል፡፡
ይሁን እንጂ ተቋሙ በዕድሜው ልክ ተገቢውን የዓይን ብሌን ልገሣ ማግኘት አለመቻሉን ነው ዋና ዳይሬክተሩ ያስገነዘቡት።
በዘርፉ የሚስተዋለውን ችግር ለመቅረፍም አጋር አካላት አሥፈላጊውን እገዛ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በሰለሞን ይታየው