አዲስ አበባ፣ ሕዳር 22፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓል ለሀገር ገፅታ ግንባታ የላቀ ሚና አለው ሲሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር አስገነዘቡ፡፡
“ሀገራዊ መግባባት ለኅብረ-ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሐሳብ 19ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በኦሮሚያ ክልል ደረጃ በአምቦ ዩኒቨርሲቲ ተከብሯል፡፡
አፈ-ጉባዔ አገኘሁ በአከባበሩ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን መከበር ለሀገር ገፅታ ግንባታ የላቀ ሚና አለው ብለዋል።
በዓሉ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች የእርስ በርስ ትውውቅና የባህል ልውውጥ መድረክ መሆን መቻሉንም ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም የክልሎች መሠረተ-ልማትና ኢንቨስትመንት እንዲነቃቃ ብሎም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከዳር እንዲደርስ ትልቅ ሚና ተጫውቷል ማታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ሰላሟ የፀናና የበለፀገች ሀገርን ለመፍጠር ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን እንዲጠብቁም ጥሪ አቅርበዋል።
19ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በዓል በሀገር አቀፍ ደረጃ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አርባ ምንጭ ከተማ ሕዳር 29 ቀን 2017 ዓ.ም ይከበራል።