የሀገር ውስጥ ዜና

በኦሮሚያ ክልል መንግስትና በኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት መካከል የተፈረመው ስምምነት ሊበረታታ የሚገባው ነው – አቶ አደም ፋራህ

By Mikias Ayele

December 01, 2024

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 22፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል መንግስት እና በኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት ክንፍ መካከል የተፈረመው የሰላም ስምምነት እጅግ ሊበረታታ የሚገባው ነው ሲሉ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፋራህ ገለጹ።

በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት እና በኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት ክንፍ ከፍተኛ አመራር ጃል ሰኚ ነጋሳ መካከል በዛሬው እለት የሰላም ስምምነት ተፈርሟል።

የስምምነቱን መፈረም አስመልክቶ አቶ አደም ፋራህ በማህበራዊ ትስስር ባስተላለፉት መልዕክት፤ ስምምነቱ እጅግ ሊበረታታ የሚገባውና እንደ ሀገር ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ ለምናደርገው ጥረት ከፍተኛ አስተዋፆ የሚያበረክት ነው ብለዋል።

እንደ ብልፅግና ፓርቲ ሰላም ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን ተገንዝበን እራሳችንን ለንግግር፣ ለድርድር እና ለትብብር ክፍት አድርገናል ሲሉም ገልጸዋል።

ህብረተሰቡ በተደጋጋሚ የሚያቀርባቸው የህግ የበላይነት መከበር ጥያቄዎች በሙሉዕነት እንዲመለሱ ለማድረግም የተጀመሩ ተስፋ ሰጪ ጥረቶችን ይበልጥ አጠናክሮ መሄድ እንደሚገባ የፓርቲው እምነት መሆኑን አመልክተዋል።

ባለፉት አመታት በሀገራችን የትኛውም የፖለቲካ ልዩነት በንግግር እንጂ በአፈሙዝ ኃይል በዘላቂነት ሊፈታ እንደማየይችል በተደጋጋሚ ታይቷል ነው ያሉት።

በየትኛውም የሀገራችን ክፍል የሚገኙ ታጣቂዎች አሁንም ቢሆን የተሻለው አማራጭ ሰላማዊ መንገድ መሆኑን ተገንዝበው በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለመንቀሳቀስ ምርጫቸው እስካደረጉ ድረስ እንደ ብልፅግና ፓርቲ የሚጠበቅብንን ድርሻ ለመወጣት ሁሌም ዝግጁ መሆናችንንም ጭምር በዚህ አጋጣሚ ለመግለፅ እወዳለሁ ብለዋል በመልዕክታቸው።