የሀገር ውስጥ ዜና

የደሴ ከተማ የኮሪደር ልማት ከአዲስ አበባ ልምድ በመቅሰም በጥራት እየተከናወነ ነው – አቶ ጃንጥራር አባይ

By Meseret Awoke

December 05, 2024

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 26፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የደሴ ከተማ የኮሪደር ልማት ከአዲስ አበባ ልምድ በመቅሰም በጥራት እየተከናወነ ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ ገለጹ።

የደሴ ከተማ የኮሪደር ልማት አስተባባሪ አቶ ጃንጥራር አባይ የከተማዋ የኮሪደር ልማት የስራ እንቅስቃሴ የሚገኝበትን ሁኔታ ተመልክተዋል።

በጉብኝታቸውም የኮሪደር ልማት ስራው አበረታች መሆኑን ገልጸው፤ የኮሪደር ልማቱ አጀማመር በጥሩ ሁኔታ ላይ የሚገኝ ነው ብለዋል።

የኮሪደር ልማቱ ከአዲስ አበባ ልምድ በመውሰድ ጠንክሮ ለመስራት ጥረት እየታየበት መሆኑን ገልጸው፤ አመራሮች፣ ባለሙያዎችና ማህበረሰቡም የበለጠ ተቀናጅተው የኮሪደር ልማቱ ለውጤት እንዲበቃ መሥራትም እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የደሴ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ በበኩላቸው፥ የኮሪደር ልማት ስራው በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ የማንፈጽመውን አንጀምርም ብለዋል።

በቅድሚያ የሚሰራው የእግረኛ እና የሳይክል መንገዶች፣ የአረንጓዴ ልማት እና የመሀል አስፋልት መንገድ ግንባታ እንደሆነና ስራውም በጊዜ እየተለካ የሚፈጸም መሆኑን አመልክተዋል።

ህብረተሰቡ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር ሠላምን በማፅናት ልማቱ እንዲፋጠን በቅንጅት እንዲሰራም ጠይቀዋል።

በአለባቸው አባተ