የሀገር ውስጥ ዜና

እየተተገበረ ያለው ሁሉን አቀፍ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ለኢኮኖሚ ዲፕሎማሲው መነቃቃት ፈጥሯል- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

By Meseret Awoke

December 05, 2024

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ እየተተገበረ ያለው ሁሉን አቀፍ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ለኢኮኖሚ ዲፕሎማሲው መነቃቃት መፍጠሩን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው በወቅታዊ፣ አካባቢያዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም ፥ በኢትዮጵያ እየተተገበረ ያለው ሁሉን አቀፍ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በተለይ በቅርቡ የተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ለኢኮኖሚ ዲፕሎማሲው አዲስ መነቃቃት መፍጠሩን ገልጸዋል።

የእስያ መሰረተ ልማት ኢንቨስትመንት ባንክ በታዳሽ ኃይል ግንባታ፣ ቀጣናውን በኃይል መሰረተ ልማት ለማስተሳሰር ኢትዮጵያ የነደፈቻቸውን ፕሮጀክቶችን ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን የባንኩ ፕሬዚዳንት በቅርቡ ባደረጉት ጉብኝት ማረጋገጣቸውን አንስተዋል።

ባለፉት ጥቂት ሣምንታት ውስጥ ከዘጠኝ ሀገራት በላይ የተውጣጡ በድምሩ ከ20 በላይ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ለመሠማራት የቅድመ ኢንቨስትመንት ጉብኝት ማድረጋቸውን አብራርተዋል።

በኢነርጂ መሠረተ-ልማት ፣የግብርና፣ የማኑፋክቸሪንግ፣ የኢንፎርሜሽንና ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ፣ የማዕድን እና የቱሪዝም ዘርፎች ላይ ለመሰማራት ፍላጎት እንዳሳዩም አምባሳደሩ ገልጸዋል።

ቃል አቀባዩ በፖለቲካ ዲፕሎማሲም ባለፉት ጥቂት ሣምንታት ውስጥ የሁለት ሀገራት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እና የዘጠኝ ሀገራት ከፍተኛ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለስልጣናት በኢትዮጵያ ጉብኝት ማድረጋቸውን አንስተዋል።

አምባሳደር ነብያት እነዚህ ጉብኝቶች ኢትዮጵያ በቀጣናው ያላት የፖለቲካ ዲፕሎማሲ ተሰሚነት እየጨመረ መምጣቱን የሚያሳይ ነው ብለዋል።

ቃል አቀባዩ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ቀንድና ለአካባቢው ከፍ ሲልም ለዓለም ሰላም እና ደህንነት የምትጫወተው ሚና ልዩ ትኩረት እንደተሰጠው የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።

በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲና ሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ የሰጡ ሲሆን ፥ ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ወቅታዊ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ዙሪያም የኢትዮጵያን አቋም መግለጻቸውን ከሚኒስቴሩ ያገነነው መረጃ ያመላክታል።