የሀገር ውስጥ ዜና

የነገ መሪዎችን መገንባት የሚጀምረው ዛሬ በሚሰራ ስራ ነው – ም/ጠ/ሚ ተመስገን ጥሩነህ

By Meseret Awoke

December 05, 2024

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የነገ መሪዎችን መገንባት የሚጀምረው ዛሬ በሚሰራ ስራ ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ሃሳብ፥ ሀገር በቀልና ችግር ፈቺ የአመራርነት ብልሃትን የምንቀስምበት እንዲሁም ትብብርና ወንድማማችነትን የምናጎለብትበት በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች የሚሳተፉበት “ነጸብራቅ የመሪነት ኮንፈረንስ”ን አስጀምረናል ብለዋል፡፡

በዚህም ሀገርን ወደ ልዕልና የሚያሸጋግሩ ተተኪ አመራሮችን የማፍራት ጥረታችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የነገ መሪዎችን መገንባት የሚጀምረው ዛሬ በሚሰራ ስራ ነው በማለት ገልጸው፤ ይህም በትውልዶች መካከል የመሪነት ጥበብ፣ ዕውቀት፣ ክህሎትና የተግባር ቁርጠኝነትን ለመታጠቅ በነባሩና በተተኪ ወጣት አመራሮች መካከል የዕውቀትና የልምድ ሽግግር ማረጋገጥ እንደሚጠይቅ ጠቁመዋል።

የዛሬው ጉባኤ ከአንድ ክስተት በላይ የሆነ የተግባር ምልክት ነው፤ በመሆኑም መሪዎቻችንን ብሔራዊ ግቦቻችን ለመምራት የሚያስፈልጋቸውን ዕውቀትና መሳሪያዎች ለማስታጠቅ እንዲሁም መሪነት በዋናነት ለማገልገል የሚወሰድ ሃላፊነት መሆኑን ማስታወስ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ስለዚህም ሀገራችንን ወደፊት ለማራመድ አቅም የሚሆኑ መሪዎችን ለማፍራት እና ለመቅረጽ የአብሮነት ህብረታችን መሰረታዊ ጉዳይ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡